በዩኒቨርሲቲው በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በበጀት ዓመቱ የተካሄዱ የምርምር ሥራዎች የመስክ ምልከታ የባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰኔ 07/2011 ዓ.ም ተደርጓል፡፡
አርባ ምንጭንና አካባቢዋን በመሰሉ ቆላማና ሞቃታማ የአየር ንብረት አካባቢዎች የሚስማሙና የተሻለ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የጥርጥሬና የቅባት እህል  የበቆሎ፣ አተር፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ አኩሪ አተርና ለውዝ ዝርያዎች የተገኙ የምርምር ውጤቶች ተመልክተዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የአትክልትና ለምግብነትና አካባቢ ጥበቃ የሚያገለግሉ ዛፍ ዝርያዎች ዙሪያ የቃሪያ፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን እንዲሁም የሞሪንጋ (ሽፈራው)፣ ወይበታና ካሳቫ ዝርያዎችም በምርምሩ ተካተዋል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የተሻለ  የሥጋና ወተት ውጤት የሚሰጡ ምርጥ ከብቶችን ከአካባቢው ጋር በማላመድ ላይ ትኩረት ያደረጉ የሙከራ የምርምር ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑ በጉብኝቱ ታውቋል፡፡  የምርምር ሥራዎቹ በመምህራን አማካሪነት በተመራቂ ተማሪዎች፣ በመምህራንና በዘርፉ ተመራማሪዎች የተሰሩ ናቸው፡፡
የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንዳሉት ምልከታው ከባለፉት 3 ምልከታዎች ጋር ሲነፃፀር በተለይ በተማሪዎች የተሰሩት የምርምር ውጤቶች ተስፋ ሰጪና አበረታች  መሆናውን  ጠቅሰው ቀጣይ የሀገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎች በክፍል የሚማሩትን በምርምርና በተግባር ማሳየታቸው ይበልጥ ሊበረታታና ወደ ሌሎች የምርምር መስኮችም ሊስፋፋ የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በተለይ ተማሪዎች በምርምሮች መሳተፋቸው ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱና ወደ ሥራ ዓለም ሲሰማሩ ውጤታማና በምርምር የታገዘ ሥራ እንዲያከናውኑ በማድረግ ረገድ ጎላ ያለ አሰተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የዩኒቨሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ በበኩላቸው የመስክ ጉብኝቱ ዓላማ በዓመቱ ውስጥ በግብርናው መስክ የተሰሩና በሂደት ላይ የሚገኙ  የምርምር ስራዎችን ከዩኒቨርሲቲውና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያሉበትን ደረጃ በመገምገምና አስተያየት በመስጠት ሥራዎቹ ውጤታማና የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚቀይሩ እንዲሆኑ ለማስቻል ታልሞ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ይስሀቅ ከቸሮ እንደተናገሩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለምርምርና ጥናት የተለወጠ ሀገር እንደሌለ ጠቅሰው የአንድ ሀገር ዕድገትን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ምርምሮችን ማካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡   የግብርና  ክፍለ-ኢኮኖሚም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ በዘርፉ ሰፋፊና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች ሊደረጉ ይገባል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በግብርናው ትምህርት መስክ የሚመረቁ ተማሪዎች ጠንካራ ምርምሮችን ሰርተው ከሀገሪቱ የግብርና ፖሊሲ አኳያ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ የተሻሉ ሀሳቦችን ማቅረብ የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ኮሌጃቸው ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነም ዶ/ር ይስሀቅ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ይስሀቅ ማብራሪያ የምርምር ውጤቶቹን ለአርሶ አደሩ ከማስተላለፋችን በፊት ከመስክ ምልከታው  የምናገኛቸውን ሀሳቦችና  አስተያየቶች በማካተትና ማስተካከያዎች ከተደረጉ በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ለማሸጋገር እንሠራለን ብለዋል፡፡
የመስኩ ተመራማሪና መምህር የሆኑት ረ/ፕ ቱማ አየለ በበኩላቸው ከተማሪዎቻቸው ጋር  በመሆን በበቆሎ  ምርታማነትና በማዳበሪያ አጠቃቀም ዙሪያ ጥናት እንዳደረጉ ገልፀው  በምርምሩ በተደረገው የአፈር ጥናት  የአካባቢው አፈር የናይትሮጅን እጥረት ቢኖርበትም የፎስፈረስ መጠኑ የተሻለ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል፡፡ አርሶ አደሩም በምርቱ መጨረሻ አካባቢ የፎስፈረስ ንጥረ ነገርን ቢጠቀም የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚችል በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡
በመስክ ጉብኝቱ  የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ ከጋሞ  ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ፣ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ ግብርና ምርምር ማዕከልና ከአርባ ምንጭ ከተማ ግብርና ጽ/ቤት የመጡ ከፍተኛ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት