Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ከጃፓይጎ(Jhpigo) ኢትዮጵያ ጋር በመተባባር ባጎለበቱት የሥርዓተ ትምህርት መቆጣጠሪያና አተገባበር ቴክኖሎጂ  ዙሪያ ሚያዝያ 11/2016 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የኮሌጁ መምህራን ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያበለጸጉትን የትምህርት ሥራ መደገፊያ ለመመልከትና አዳብሮ ለሌሎች ተቋማት ተደራሽ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመነጋጋር ውይይቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደ መሆኑ ከትምህርት አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ፈተና ድረስ በቴክኖሎጂ ተደግፎ መስጠት ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ወጪ ለመቀነስና ሥራን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ የተናገሩት ዶ/ር ዓለማየሁ ይህንን በተመለከተ ኮሌጁ የሠራው ሥራ የሚበረታታና በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የሥርዓት አቅም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ በትምህርትና ጤና ዘርፍ እንደ ሀገር ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረው በመምህራኑ የተሠራው ዲጂታል ቴክኖሎጂ አንድ መምህር ክፍል መግባቱንና ማስተማሩን፣ የትምህርቱን ይዘት፣ የመምህራንና ተማሪዎች የክፍል ውስጥ ግንኙነትና በአጠቃላይ የመማር መስተማር ሁኔታን ማወቅ የሚቻልበት በመሆኑ ይበልጥ ዳብሮ ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂው ባለቤትነቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የጃፓይጎ ኢትዮጵያ ሆኖ በጤና ሚኒስቴር የተወሰኑ ማስተካከያዎች በጋራ ተደርገው ሌሎች ተቋማትም ሥልጠና ወስደው የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በጋራ እንደሚሠሩ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ዘርይሁን ዘርዶ የሥርዓተ ትምህርት ጥራት መቆጣጠሪያው በኮሌጁ መምህራን ሃሳብ አመንጪነት ከጃፓይጎ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የጎለበተ ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረው ቴክኖሎጂው በ2016 ዓ/ም ወደ ተግባር በመግባቱ በኮሌጁ ጥሩ ውጤት ማምጣት መቻሉንና ጤና ሚኒስቴር ተሞክሮውን በማዳበር ለተለያዩ ተቋማት አካፍሎ በትምህርት ጥራትና በሰው ኃይል ላይ ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ታስቦ ውይይቱ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

የኮሌጁ የተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ አስተባባሪ ረ/ፕ አብነት ገ/ሚካኤል ‹‹AMU CMHSC-Digital Learning and Quality Improvement Initiatives›› በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ሲያቀርቡ እንደገለጹት በኮሌጁ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ የሚባክን የትምህርት ክፍል መኖሩን መገንዘባቸው መነሻ ምክንያት ሆኗቸው እንዴት ማስተካከልና የትምህርት ጥራትን ማስጠብቅ እንደሚቻል ከኮሌጁ መምህራን ጋር በመወያየትና ከጃፓይጎ ኢትዮጵያ ጋር በመተባባር ጂጂታል ቴክኖሎጂውን አጎልብተዋል፡፡ ቴክኖሎጂው በ2016 ዓ/ም ተተግብሮ በኮሌጁ የተለያዩ ት/ክፍሎች ጥሩ ውጤት መገኘቱን እና ቴክኖሎጂው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ማግኘት የሚገባቸውን በሥርዓተ ትምህርቱ የተካተቱ ኮርሶች በሙሉ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት