Print

የፌዴራል ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን የፌዴራል የመንግሥት ተቋማትን የግዥ ሥርዓት ለማሻሻልና ለማዘመን  በ“Electronic Government Procurement /eGP” ዙሪያ ለዘርፉ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቲዎሪና በተግባር የተደገፈ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ከጳጉሜ 2-4 /2015 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በሀገር አቀፍ ደረጃ የግዢ ሥርዓትን ነጻና ግልጽ ለማድረግና ለማዘመን እንደ ሀገር በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ግዢ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት እንዲፈጸም ተቋማት ሥልጠና ወስደው ወደ ትግበራ እንዲገቡ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ተሟልተው  እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ጨረታዎች ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓት (eGP) እንደሚሆኑ ም/ፕሬዝደንቷ የጠቆሙ ሲሆን ይህን የግብይት ሂደት መጠቀም በከፍተኛ ደረጃ ለወረቀትና ለጋዜጣ ግዢ የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ጊዜ ቆጣቢና የተቋማትን ውስብስብ የብሮክራሲ ሥርዓት በማስቀረት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦው ከፍተኛ  መሆኑን ወ/ሮ ታሪኳ ተናግረዋል፡፡  

በፌዴራል ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ፕሮጀክት የቢዝነስ ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ወንድወሰን ወንጀሎ  በተለይ  ተቋማት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን በመጠቀም ጥራት ያለው ግዢ እንዲፈጽሙ ግንዛቤ ለመፍጠር  የተዘጋጀ ሥልጠና  መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ወንድወሰን ከዚህ ቀደም በሦስት ክላስተር ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችና የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክ ግዢ ሂደትን የተመለከተ ሥልጠና መሰጠቱን አውስተው መሥሪያ ቤቶቹም በጥራትና በብቃት ሂደቱን በመከተል ግዢ መፈጸም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ትልቅ በጀት የሚመሩ ሴክተሮች ይህንን የግብይት ሥርዓት በመጠቀም አላግባብ ወጪን እንደሚከላከሉ፣ ውጤታማ የግዢ ሂደትን ለመዘርጋት እንደሚችሉና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንደሚያግዛቸው ቡድን መሪው ጠቁመዋል፡፡

የ“eGP” ምንነትና ግዥ የሚመራባቸው ሕጎችና መመሪያዎች፣ ግዥና የኤሌክትሮኒክ ግዥን የሚፈጽሙ ተቋማት ምን ዓይነት ናቸው በሚሉና የ“eGP” ሲስተም የመጠቀም አስፈላጊነት እንዲሁም እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ዓመታዊ የግዥ ፍላጎቱን በኤሌክትሮኒክ የግዢ ሥርዓት በምን መልኩ ማቅረብ ይችላል የሚሉት ሥልጠናው ትኩረት ያደረገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሥልጠናውን የዩኒቨርሲቲው ግዥና ንብረት አስተዳደር፣ ፋይናንስና በጀት አስተዳደር፣ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ግምገማ፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ውሃ  ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንዲሁም የሁሉም ካምፓስ ግዥና ንብረት አስተዳደተር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች ታሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት