Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዝደንቶችና በፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሥር ያሉ ዳይሬክተሮች የ2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ ዕቅድ መስከረም 24/2016 ዓ/ም ተፈራርመዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የበጀት ዕቅዱ ስትራቴጂክ ዕቅዱን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን የትምህርት አመራርና አስተዳደር ጥራትን በማጠናከር የተቋሙን አቅምና ብቃት ማሳደግና ውጤታማ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም በሁሉም የሥራ ክፍሎች የበጀት ዓመቱ ዕቅድ እስከ ግለሰብ ድረስ ወርዶ መታቀዱ ዕቅዱን ለመፈጸም ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ይፍሩ በበኩላቸው የበጀት ዓመቱ ዕቅድ በዋናነት ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው የስትራቴጂክ ዕቅድ መካከለኛ ጊዜ (ከ2016-2018 ዓ/ም) የ3 ዓመት ዕቅድ መሠረት የ2016 ዓ/ም ዕቅድን በመለየት ከተዘጋጀ በኋላ በካውንስል አባላትና በአስተዳደር ቦርድ ጸድቆ የሚመለከታቸው አካላት መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡ ዕቅዱን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ በአካዳሚክ ዘርፍ እስከ መምህራን፣ በምርምር ዘርፍ እስከ ተመራማሪው እንዲሁም በአስተዳደር ዘርፍ እስከ ክፍል ሠራተኛው ድረስ ሸንሽኖ በማውረድ በትጋት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የዓመቱ ሥራ አፈፃፀም በየሩብ ዓመቱና በዓመቱ መጨረሻ እንደሚገመገምም ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት