Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ /ICT/ ዳይሬክቶሬት በሥራ ክፍሉ ለሚገኙ ከየካምፓሱ ለተወጣጡ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ጀማሪ ባለሙያዎች  በኮምፒውተር ማሽን ጥገና  እና በሲስተም ዴቨሎፕመንት አስተዳደር ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኢያሱ ዲላ ሥልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎች በአይሲቲ ዙሪያ ያላቸውን ክሂሎት ለማሳደግ እንዲሁም ቴክኒካል ዕውቀት እንዲኖራቸው ለማስቻል ታልሞ መሰጠቱን ገልጸው ያገኙትንም ልምድና ዕውቀት ሥራ ላይ እንዲያውሉት አሳስበዋል፡፡ ከሥልጠናው ያገኙትንም ዕውቀት ለመለካት የተግባር ፈተና እንደሚሰጣቸውና ፈተናውን ያላለፉ ሠልጣኞችም ዳግም ሥልጠና እንዲወስዱ የሚደረግ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረው በቀጣይም የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የአይሲቲ ሶፍትዌር ፕሮግራመርና አሠልጣኝ አቶ ችሮታው ከንቲባ በኦፕን ሶርሶች፣ በሲስተም ዴቭሎፕመንትና አድሚኒስትሬሽን ላይ ያሉ እና አዳዲስ  የሆኑ ሶፍትዌሮችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሥልጠናውም ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ሂደት የሚፈጠረውን የአቅም ውስንነት ለመቅረፍ፣ ወጪን ለመቀነስና የሰዓት ብክነትን ለማስቀረት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡  

ሌላኛው አሠልጣኝ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የሜይንቴናንስ ሲኒየር ባለሙያ አቶ እሱያውቃል አወቀ  የቢሮ ዕቃዎችን፣ የኮፒ ማሽኖችን፣ ፕሪንተሮችን፣ ኮምፒውተሮችን እንዲሁም  ላፕቶፖችን፣ ፋክስ እና ፓወር ቦርዶችን መጠገን የሚያስችል ሥልጠና የሰጡ ሲሆን ይህም በቀጣይ ውጤታማ የሆነ ሥራ እንዲሠራና የተግባር ልምድ እንዲኖር ያግዛል ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በቴክኒካል ክሂሎት ዙሪያ ያለባቸውን ክፍተት በመቅረፍ የተግባር ልምዶችን የወሰዱበት እንዲሁም ለቀጣይ ሥራቸው የሚረዳ ግብዓት ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት