Print

በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅ/ጽ/ቤት ለአርባ ምንጭና ጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች የፋይናንስና ግዥ ባለሙያዎች፣ ኦዲተሮች እና የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች በታክስ ሕግና መመሪያ ዙሪያ ጥቅምት 15/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ልዩ ረዳት አቶ ዮሴፍ ወርቁ እንደተናገሩት መንግሥት የሚያወጣቸው የተለያዩ መመሪያዎችና አዋጆች የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን ስኬታማና በዕውቀት የተመራ እንዲሆን የሚያግዙ በመሆኑ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ወደ ተግባር ሊቀይሩት ይገባል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ከሚፈጽሟቸው ግዥዎች እንዲሁም ከተቀጣሪ ሠራተኞች የሚሰበሰበው ገቢ ለሀገር እድገት ትልቁን ድርሻ የሚጫወት በመሆኑ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ጠለቅ ያለ ግንዛቤ መፍጠር የሥልጠናው ዓላማ መሆኑን በገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅ/ጽ/ቤት የታክስ ትምህርትና ሥልጠና ባለሙያ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ጫሻ ገልጸዋል፡፡

እንደ ባለሙያዋ በቅጥር ከሚገኝ ደመወዝ፣ ለሠራተኛው ከሚሰጥ ጉርሻ፣ አበል፣ የመልካም ሥራ ማበረታቻ ገንዘብ እንዲሁም በቀጣሪውና በተቀጣሪው ሠራተኛ ስምምነት ከሚከፈል የሥራ ማፈላለጊያ ገንዘብ በሠራተኛ ቅጥር ሂደት የታክስ ገቢ ከሚሰበሰብባቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ቀጣሪው ክፍል ቀጥሮ የሚያሠራው ሠራተኛ ድንገተኛ ሕመም ቢገጥመው ተቋሙ ከሚያወጣው የሕክምና ወጭ እንዲሁም ተቀጣሪው ሠራተኛ የተለያዩ የሥልጠናና የትምህርት እድል ተጠቃሚ ቢሆን የሚወጣው ወጭ ግብር ከማይሰበሰብባቸው ነጻ አገልግሎቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 መመሪያ መሠረት ማንኛውም ገቢ የሚያገኝ ሰው ግብር የመክፈል ግዴታ ያለበት ሲሆን ወርሃዊ የደመወዝ መጠኑ 600 ብር ብቻ ከሆነ የመንግሥት ሠራተኛና 30 ቀን ሙሉ በሥራ ላይ ካልቆየ የጉልበት ሠራተኛ ግብር መሰብሰብ አዋጁ አይፈቅድም፡፡

በታክስ ሕግና መመሪያ ዙሪያ የሚወጡ አዋጆች በቂ ዕውቀትና ክሂሎትን  የሚጠይቁ በመሆናቸው መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ሠልጣኞች ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት