Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በአርባ ምንጭ ከተማ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ተቋም ውስጥ ላሉ ተጠርጣሪዎች፣ ወጣት ጥፋተኞች እንዲሁም ታራሚዎች በተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች አያያዝ ዙሪያ ኅዳር 18/2016 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው በጋሞና ጎፋ ዞኖች የታራሚዎች፣ ተጠርጣሪዎችና ወጣት ጥፋተኞች አያያዝን በተመለከተ በሕግ ትምህርት ቤት መምህራን የተዘጋጀውን ግራድ የምርምር ፕሮጀክት ውጤት መሠረት ያደረገ ሲሆን ዓላማውም ተጠርጣሪዎች መብቶቻቸውን በሕገ-መንግሥቱም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ በተቀመጠው ልክ እንዲጠይቁና እንዲጠቀሙ ማስቻል መሆኑን የፕሮጀክቱ ተመራማሪ መ/ር ዳግም ወንድሙ ገልጸዋል፡፡

የሕግ ጥሰቶች የሚከሰቱት በመርማሪ ፖሊሶች ግንዛቤ ማነስ፣ ቸልተኝነትና በሚጠቀሙባቸው የምርመራ ቴክኖሎጂዎች ያልዳበሩ መሆን እንዲሁም በወንጀሎች ውስብስብነት ሲሆን የሕግ ጥሰትን ለማስቀረት ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች የመናገርና የመጠየቅ መብቶቻቸውን አውቀው እንዲጠቀሙበት ብሎም ፖሊሶች መብቶቻቸውን ሊያከብሩላቸውና ሊጠብቁ እንደሚገባ መ/ር ዳግም አክለዋል፡፡ በፖሊሶች ምክንያት የሚነሱ የሕግ ጥሰቶችን ለመቀነስ ያስችል ዘንድ በቀጣይ ለባለድርሻ አካላት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡

የግራንድ ፕሮጀክቱ ተመራማሪ የሆኑት ሌላኛው አሠልጣኝ መ/ር አብርሃም ክንፈ ተጠርጣሪዎች ስለወንጀል ፍትሕ ሥርዓተ ሕግ በተገቢው ሁኔታ የማያውቁ በመሆኑ ያላቸውን መብት ተናግረው ማሳመን አይችሉም ብለዋል፡፡ በመሆኑም አንድ ተጠርጣሪ ስለመብቱ እንዲያውቅ በማድረግ እንዲሁም ተጠርጣሪው በሕግ ከለላ ሥር ከዋለ በኋላ በሰብአዊነቱ ሊከበርና በሥርዓቱ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ለፍርድ ቀርቦ ተገቢውን ውሳኔ ሊያገኝ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ ሕግን እየጠበቁ ወንጀልን መከላከልና የተጠርጣሪዎችን መብት የማስከበርና የማክበር ሥራ አብሮ ሊሠራ እንደሚገባም መ/ር አብርሃም ተናግረዋል፡፡

የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች መብቶች፣ በተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች ላይ የሚፈጠሩ የሕግ ጥሰቶች እና በዚህ ረገድ ከሕግ አካላት የሚጠበቁ ተግባራት በሥልጠናው ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA