Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ ጋር በመተባበር ከጋሞ ዞንና ወረዳዎች ለተወጣጡ ከፍተኛ መኮንኖችና የዲቪዥን ኃላፊ ሴት አመራሮች የአመራርነት ሚናን ለማጎልበት ከኅዳር 19-20/2016 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው የአመራር ምንነት፣ የጥሩ መሪ መገለጫ ባህሪያት እንዲሁም ራስን፣ ቡድንና ተቋምን መምራት የሚሉ ርእሰ ጉዳዮች በስፋት ተዳሰዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ኦኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ የተቋሙን ራእይ ለማሳካት በተቋምና በኮሌጅ ደረጃ በርካታ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው በምርምር በተለዩ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ እና ከሌሎች ተቋማት በሚመጡ ፍላጎቶች ላይ በመመርኮዝ በሁለት መልኩ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ የአመራርነት ሥልጠናውም በሥራ አጋጣሚ ያገኙትን ልምድ ከሳይንሱ ጋር በማጣመር የተሻለና ወቅቱ የሚፈልገውን የአመራር ሚና ለመወጣት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊና አሠልጣኝ መ/ት አስቴር ሰይፉ በሀገር ደረጃ የሴቶች ቁጥርና ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሴቶች በሚሠሩበት የሥራ ዘርፍ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው ለማብቃትና ክሂሎታቸውን ለማሳደግ ታልሞ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት ሙሉ ሀገራዊ የሆነ እድገት ለማስመዝገብ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት አሠልጣኟ ሥልጠናው በግልም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ራሳቸውን እንዲያበቁ ብሎም ከራስ አልፎ ቡድንና ተቋምን መምራት እንዲችሉ የሚያበቃቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህርና አሠልጣኝ ቢክስ ሰጠኝ በሥልጠናው የአመራር ምንነት እና በአመራርነት ወቅት ያለው ሂደት እንዲሁም የጥሩ መሪ መገለጫ ባህርያት በስፋት መዳሰሳቸውን ገልጸው በጸጥታው ዘርፍ ያሉ አመራሮች የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ያላቸው ሚና ጉልህ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ የተሻለ የአመራርነት ክሂሎት እንዲሰጡ ማስቻልና ማብቃት  ለሀገር ኢኮኖሚ፣ ለማኅበራዊ ደኅንነትና ለሕግ አፈጻጸም ብሎም ለፍትሕ ትልቅ ተጽዕኖ ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አሠልጣኙ አክለውም አመራር ከተመሪው በተሻለ ዕውቀት ያለውና አስፍቶ የሚያይ አከባቢውን የሚረዳ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ 

የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ደበበ አኒቶ እንደ ተቋም የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ሥልጠናው እንዳስፈለገ ጠቅሰው ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት በምግባር የታነጸ ተተኪን ለማፍራት ብሎም ቀልጣፋና ፈጣን ፍትሕ የሰፈነበት ተቋም ለመገንባት ማዋል እንደሚገባቸው በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ ለቀረበው የሥልጠና ጥሪ ዩኒቨርሲቲው ለሰጠው ፈጣን ምላሽም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ከአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር ቡድን መሪ ም/ኢንስፔክተር ሠልጣኝ ሰርካለም ሰበረው ሥልጠናው ያለን ዕውቀት ላይ ተጨማሪ አቅም የፈጠረልንና የምንመራውን ሕዝብና ተቋም በብቃት ለመምራት አቅም የሰጠን ነው ብለዋል፡፡ በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ለተቋማቸው አባላት ለማካፈል ኃላፊነት መውሰዳቸውን የተናገሩት ሠልጣኟ መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው ቢቀጥሉ መሥራት የሚችሉ ሴቶችን በማበረታታት አቅም ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ ሠልጣኝ የምዕራብ ዓባያ ወረዳ ፖሊስ ም/ኢንስፔክተር ዘውዲቱ ኤርሚያስ ሥልጠናው የአመራር ምንነት፣ አካሄድና አሠራር ላይ ግንዛቤን እንደፈጠረላቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ያገኘሁትን ልምድ በማጎልበት በቀጣይ በወረዳዬ ያሉ ሴት ፖሊስ አባላትን የማብቃትና የመደገፍ ሥራ ለመሥራት ብሎም ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ መሪ ለመሆን ሙሉ ዝግጁ ነኝም ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማብቂያ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት እንዲሁም ከዞኑ ፖሊስ መምሪያ ለዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እና ለአሠልጣኞች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት