Print

‹‹Human Bridge›› የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ታኅሣሥ 01/2016 ዓ/ም የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግዙፍ እንደመሆኑ አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት ከዚህ ቀደም ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶች በግዢና በድጋፍ ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ‹‹ሂዩማን ብሪጅ›› ከተሰኘ የስዊድን ግብረ ሠናይ ድርጅት የሆስፒታል አልጋዎች፣ ስትሬቸር፣ የላቦራቶሪ ወንበሮች፣ የሕፃናት ማሞቂያዎች፣ ዊልቸር፣ የሕክምና አልባሳትና የመሳሰሉ ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው ከፍተኛ የበጀትና የውጪ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ግዢውን ማጠናቀቅ ከባድ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው ባለው አቅም ሪፈራል ሆስፒታሉን በቁሳቁስና አስፈላጊ ግብአቶች ለማሟላት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝና በከፊል ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ የሕክምና ዕቃዎች በመግባት ላይ መሆናቸውን ወ/ሮ ታሪኳ ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቷ ለሂዩማን ብሪጅ ካንትሪ ዳይሬክተር እንዲሁም በስዊድን ሀገር ለሚገኙ የዘርፉ ኃላፊዎች በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በበኩላቸው 600 የተኝቶ ሕክምና አልጋዎችን የሚይዘውን ግዙፍ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ በማጠናቀቅ ግብአቶችን አሟልቶ ወደ ሥራ ለመግባት ከሀገሪቷ አሁናዊ ተጨባጭ የገበያ ሁኔታ አንጻር ከባድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከረጂ ድርጅቶች ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶች የገቡ ቢሆንም ካለው ፍላጎት አኳያ በቂ አለመሆኑን ዶ/ር ደስታ አክለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት