Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታልና ‹‹Hope of Light›› የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ተቋርጦ የነበረውን የማሕጸን ፌስቱላ ሕክምና ዳግም ለማስጀመር የሚያስችልና ለ10 ዓመታት የሚቆይ የመግባቢያ ስምምነት ታኅሣሥ 02/2016 ዓ/ም ተፈራርመዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የ‹‹Hope of Light›› መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል ድርጅታቸው በእናቶች ጤና በተለይም በማሕጸን ፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ላይ በማተኮር የሚሠራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ ሠናይ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ በዋናነት በሆስፒታሉ ተቋርጦ የቆየውን የማሕጸን ፌስቱላ ሕክምና አገልግሎት ዳግም ለማስጀመር ያለመ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር አምባዬ ለሥራው ያግዝ ዘንድ በሆስፒታሉ ለሚገኙ የሕክምናና ጤና ባለሙያዎች በማሕጸን ፊስቱላ ዙሪያ እንዲሁም ሕክምናውን እዚሁ መስጠት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ ብለዋል፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች በሚገኘው ማኅበረሰብ ዘንድ በሽታውን የመለየት ሥራ እንዲሁም በሽታውን ከመከላከል አንጻር አጋዥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በትብብር መሥራት ሌላኛው የስምምነቱ ትኩረት መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም እናቶች የማሕጸን ፌስቱላ ችግር ሲገጥማቸው ሕክምናውን ለማግኘት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመሄድ እንደሚገደዱና ይህም ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ እንደሚዳርጋቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ታምሩ ስምምነቱ ባለሙያዎችን በማሠልጠን ሕክምናው በሆስፒታሉ እንዲሰጥ በማድረግ ችግሩን የሚቀርፍ ሲሆን ከጋሞ ዞን ባሻገር ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የሚመጡ እናቶችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አንተነህ ካሳዬ ስምምነቱ ለአካባቢውም ሆነ ለሆስፒታሉ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ የማሕጸን ፊስቱላ ሕክምናን ከሌሎች አግልግሎቶቹ ጋር በማቀናጀት በትኩረት እንደሚሠራ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በስምምነቱ መሠረት ተቋሙ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡

ፌስቱላ በወሊድ ወቅት የምጥ ሂደቱ እንቅፋት ሲገጥመው በሚፈጠር ውስጣዊ ጉዳት በፅንሱ መተላለፊያ/በርዝ ካናል/ እና በሽንት ፊኛ መካከል ወይም በፅንስ መተላለፊያ እና ፊንጢጣ መካከል ሽንቁር ሲፈጠር የሚከሰት የጤና እክል ሲሆን በዚህ ወቅት ሽንት ወይም ዓይነ ምድር እንዲሁም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ሁለቱንም የመቆጣጠር ችግር ሊያስከትል እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት