Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሳምንት መጨረሻ መርሃ ግብር በኅብረተሰብ ጤና ትምህርት የ2 ዲግሪ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች የልማታዊ ቡድን ሥልጠና ፕሮግራምን/Developmental Team Training Program /DTTP/ መሠረት በማድረግ በአርባ ምንጭ ከተማ ጉርባ ቀበሌ የአካባቢውን ማኅበረሰብና አጋር አካላትን በማስተባበር ያስገነቡት የደረቅ ቆሻሻ መጣያና ከጤና ተቋማት የሚወጡ የሕክምና ዕቃዎች ቆሻሻ ማቃጠያ (Incinerator) ታኅሣሥ 06/2016 ዓ/ም ተመርቆ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በተማሪዎቹ የተሠራው ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ችግር በተጨባጭ ሁኔታ የሚፈታና መማር ማስተማሩ ከማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ጋር ላለው ትስስር ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ መሰል ሥራዎች በሌሎች የትምህርት መስኮችም ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የኅብረተሰብ ጤና ት/ክፍል ኃላፊ ረ/ፕ ሙስጠፋ ግላኝ እንደገለጹት በኅብረተሰብ ጤና ትምህርት የ2 ዲግሪያቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች የልማታዊ ቡድን ሥልጠና ፕሮግራምን እንደ አንድ ኮርስ የሚወስዱ ሲሆን ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው የማኅበረሰቡን ችግሮች በመለየትና ፕሮጀክት በመቅረጽ ችግር ፈቺ ሥራ የሚሠሩበት ነው፡፡ በጉርባ ቀበሌ ከጤና ተቋማት የሚወጡ የሕክምና ዕቃዎች ቆሻሻ በማኅበረሰቡ ጤና ላይ አደጋ እያስከተለ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ተማሪዎቹ ቀበሌውን መርጠው ፕሮጀክቱን መሥራታቸውን ረ/ፕ ሙስጠፋ ተናግረዋል፡፡

የት/ክፍሉ መምህርና የፕሮጀክቱ አማካሪ ረ/ፕ መስፍን ማሞ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ራሱን የቻለ ኮርስ ሲሆን ተማሪዎች በተለያዩ ትምህርቶች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር የሚለውጡበት ነው ብለዋል፡፡ የሳምንት መጨረሻ መርሃ ግብር ተማሪዎች እንደመሆናቸው በሥራ ወቅት የሚገጥማቸውን የጊዜ መጣበብና የበጀት ችግሮች አልፈው ከፍጻሜ መድረሳቸው የሚመሰገን መሆኑንም አክለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ጉርባ ቀበሌ አስተዳደር አቶ እሸቱ አበበ በአካባቢው ቀደም ሲል የተለያዩ ቆሻሻዎች በየቦታው ይጣሉ እንደነበር አስታውሰው በተማሪዎቹ የተጠናው ጥናትና የተሠራው ፕሮጀክት የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታና ከአየር ብክለት የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኅብረተሰብ ጤና የ2 ዲግሪ ተማሪ አንዷለም ሳሙኤል በሀገራችን ከሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች መካከል አብዛኛው በግልና በአካባቢ ንጽሕና ችግሮች ምክንያት እንደሚከሰቱ ተናግሮ ችግሮችን በጥናት በመለየት ተግባራዊ መፍትሔ ቢፈለግ ማኅበረሰቡን ከተለያዩ በሽታዎች መከላከል ይቻላል ብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ 88,000 (ሰማንያ ስምንት ሺህ) ብር በሆነ ወጪ የተገነባ ሲሆን ለፕሮጀክቱ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ አጋር አካላት የምስጋናና የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት