Print

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከ10 ዩኒቨርሲቲዎች ለተወጣጡ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እና የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተሮችና አስተባባሪዎች በተማሪ ልማት ዙሪያ ከጥር 16-17/2016 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሥልጠናውን ከሀዋሳና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የሥነ ባሕርይና ሥነ ልቦና ት/ክፍል የመጡ መምህራን የሰጡ ሲሆን ሥልጠናው በግለሰባዊና ማኅበራዊ ሰብእና ግንባታ እንዲሁም በትምህርት ለውጥና ከትምህርት በኋላ ለሥራ ዓለም ተዘጋጅተው እንዲወጡ በሚያስችሉ ጉዳዮች (Psychosocial, Academic and Career Development) ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የተማሪዎች ልማት ዴስክ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ማሕሌት በቀለ እንደገለጹት በሚኒስቴሩ ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ ያላቸው የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በተማሪዎች ልማት ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጥ በሆነ መልኩ ለማከናወን እንዲቻል የተማሪዎች ልማት የሥልጠና ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡ ለአፈጻጸሙም ከሥራው ጋር ቅርበት ላላቸውና ሥራውን በቀጣይነት ማስኬድ ለሚችሉ ባለሙያዎች የአሠልጣኞች ሥልጠና ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ባለሙያዋ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ባለሙያዋ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተቋማት ሲወጡና ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ሥራ ጠባቂ ሳይሆኑ የሥራ ፈጠራ አቅም እንዲኖራቸው እንዲሁም ሰብእናቸውን በማጎልበትና ክሂሎታቸውን በማሳደግ ለሀገር የሚጠቅሙ  እንዲሆኑ ለማስቻል ሥልጠናው የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ትምህርት ሚኒስቴር ሥልጠናውን ሲያዘጋጅ ተማሪዎቻችን ከሚማሩት የሙያ ዕውቀትና ክሂሎት ባሻገር ሰብእናን በመገንባት ትምህርታቸውን እንዴት በውጤታማነት መማር እንዳለባቸው ማሳወቅና ወደፊት የተሳካ የሙያ ሕይወት  እድገት እንዲኖር ማስቻል ትኩረት የሚሻ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡ ተማሪዎች በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ሥልጠናው አንዱ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ዶ/ር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ ሥልጠናው ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተቋማት ሲወጡ ሥራ ለማግኘት እንዳይቸገሩና በተሻለ ሰብእና ተቀርጸው ለሀገር ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የሥልጠናው ተሳታፊ መ/ር ሚሊዮን ደሳለኝ እንደ ሥነ ልቦና ባለሙያነታቸው ሥልጠናው ሙያቸውን የሚያግዝ፣ ተጨማሪ ዕውቀት የሚሰጣቸው እንዲሁም ለጋራ አረዳድና ልምድ ለመለዋወጥ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ሥልጠናው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በስድስት ክላስተሮች እየተሰጠ ሲሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተሰጠው ሥልጠና ሀዋሳ፣ ዲላ፣ ዋአሞ፣ ጂንካና ሌሎችንም ጨምሮ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት