Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2016 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ ክንውን ሪፖርት ጥር 17/2016 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ከዩኒቨርሲቲው ዓመታዊ ዕቅድ አንፃር የቀረበውን የግማሽ ዓመት ሪፖርት በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና ደካማ አፈፃፀም የታየባቸው መስኮችን በመለየት በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር የግምገማ መድረኩ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሰለሞን ይፍሩ ባቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና በአመራርና አስተዳደር ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ቀርበዋል፡፡

የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ሥራዎች በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የመሥራት ደረጃን ለማሻሻል በትኩረት መሥራት፣ የምርምር ሥራ ውጤቶች እና የተላመዱና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ የማሸጋገር ሥራ አጠናክሮ መሥራት፣ ከኦዲት ግኝት የፀዳ ተቋም ለመሆን በትኩረት መሥራት፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችን በማበራከትና አሠራሮችን በማሻሻል ገቢን ማሳደግ፣ ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና አዲስ የተጀመሩትን ደግሞ በብቃት እንዲሠሩ ትኩረት ሰጥቶ መደገፍ፣ የቅድመ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተና የማለፍ መጠን እንዲጨምር የመማር ማስተማር አፈጻጸም ጥራትን ማሻሻል፣ የተዘጋጀውን የዩኒቨርሲቲውን አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት ጥናት መሠረት የሠራተኛ ምደባ ሥራን በትኩረት ማከናወን በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የተማሪ ምግብ ጥሬ ዕቃን ጨምሮ የግብዓት አቅርቦት የገበያ ዋጋ ንረት በግማሽ ዓመቱ ከገጠሙ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም ከካውንስሉ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከዘርፍ ከፍተኛ አመራሮችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት