Print

አርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከኢፌዲሪ የከተማና መሠረት ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር ሀገር አቀፍ የውኃ ዘርፍ የኮንስትራክሽን ሥራዎች የሰው ኃይልና የማሽነሪዎች ምርታማነት ኖርም (Standard Productivity Norm) ላይ በጋራ ለመሥራት መጋቢት 12/2016 ዓ/ም የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ አውግቸው እንደገለጹት በኢንደስትሪ በሚሠሩ ሥራዎች ወጥና ዘመናዊ የሆነ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋትና የማማከር አገልግሎት መስጠት የተቋሙ ዋና ዓላማ ሲሆን የተቋማትና የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን መስጠት እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መለየት፣ መቀመር፣ በኢንደስትሪ ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ማስፋፋት እና የአሠራር ሥርዓቶችን ማሻሻል ላይ ይሠራል፡፡

በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ በጥቅም ላይ ያለው የምርታማነት ኖርም (Standard Productivity Norm) ከ20 ዓመት በፊት የተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ሰዓት የአሠራርና የኮንስትራክሽን ዘዴ ለውጦችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ያሉ በመሆኑ የምርታማነት ኖርም መጠናትና መከለስ ይኖርበታል፡፡ እንደ አቶ አበራ ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነውን የሙከራ ጥናት መሠረት በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደ መነሻ በተወሰኑ ከተሞች ማጥናት የተቻለ ሲሆን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በውኃ ዘርፍ የሚሠሩ የግንባታ ፕሮጀክት ሥራዎች ውጤታማነት ጥናት የሚከናወን ይሆናል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ቀደም ሲል በተፈራረሙት ውል መሠረት በውኃ ዘርፍ ግንባታ ሥራዎች የሰው ኃይልና የማሽነሪዎች ምርታማነት ኖርም (Standard Productivity Norm) በተመረጡ ቦታዎች እየሠሩ እንደሚገኝ አስታውሰው እንደ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎችን በመምረጥ መረጃ እንዲሰበስቡና በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡ የሚሰበሰበው መረጃ የተሠሩ ፕሮጀክቶችን ውጤታማነትና የጊዜ አጠቃቀም የሚያካትት ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በሀገር ደረጃ ለጥናቱ መመረጡ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ከፍአለ በበኩላቸው ቀደም ሲል ከኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ‹‹Building Information Management/BIM›› በሚል ርእስ ለቴክኖሎጂ እና ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች መምህራን፣ ለፋሲሊቲ አስተዳደር እና ለግንባታ ዘርፍ ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ በውኃ ዘርፍ የግንባታ ሥራዎች የሰው ኃይልና የማሽነሪዎች ምርታማነት ኖርም (Standard Productivity Norm) ለሚደረገው ጥናት ዩኒቨርሲቲው ለኢንደስትሪው ውጤታማነት ግብዓት የሚሆን መረጃ በመሰብሰብ እንደ ምርምር ተቋም ግዴታውን ለመወጣት ያደረገው ስምምነት መሆኑን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ ጥናቱ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪውን ውጤታማነት ከማሳደግ ባሻገር ለዩኒቨርሲቲው መማር ማስተማርና ማማከር ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት