Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሕክምና፣ ነርሲንግ፣ ሚድዋይፍሪና አንስቴዥያ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞችን በኢፌዴሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን/ Education and Training Authority/ ዕውቅና/Accreditation/ ለማሰጠት የሚያስችል የውስጥ ግምገማ አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ከታችኛው ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ከጥራት አንጻር ከፍተኛ ችግር ያለበት በመሆኑ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትኩረት የሚሰጠው አጀንዳ ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማሳካት የትምህርት ፕሮግራሞች ዕውቅና ማግኘት ዓይነተኛ ሚና ያለው መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ ለዚህም ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት፣ ጥራት ያለው የትምህርት ግብዓት፣ የሰው ኃይል፣ ቤተ ሙከራ፣ የኮምፕዩተር ማዕከል እንዲሁም ብቃት ያለው የአስተዳደር ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ ከትምህርት አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ፈተና ድረስ ያለውን ሂደት በቴክኖሎጂ ተደግፎ መስጠት ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ወጪ ቆጣቢ በመሆን ሥራን ለማቀላጠፍ ይረዳል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ኮሌጁ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ጃፓይጎ ኢትዮጵያ/Jhpigo Ethiopia/ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ፕሮግራሞችን ዕውቅና በማሰጠት ሂደት የሰው ኃይል በማሠልጠንና ስታንዳርድ እንዲዘጋጅ በማድረግ አሻራውን አሳርፏል ብለዋል፡፡ የውስጥ ግምገማው ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው ፕሮግራሞች ተሞክሮ የሚሆንና ጥሩ ግብዓት የሚገኝበት መሆኑንም ዶ/ር ደስታ ገልጸዋል፡፡

የኮሌጁ ተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ አስተባባሪ ረ/ፕ አብነት ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የውስጥ ግምገማ መድረኩ አራቱን የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች ዕውቅና ለማሰጠት የተከናወኑ ሥራዎችን ለማሳወቅና በተዘጋጁ መስፈርቶች መሠረት ገምግሞ ግብዓት ለማግኘት የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮግራሞቹ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ሲገኙ ዕውቅና እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት