Print

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመስክ ምልከታ በማድረግ እና ከተማሪ ተወካዮች የተነሱ ጥያቄዎችን አስመልክቶ በትኩረት ሊሠሩ በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል ጥር 13/2016 ዓ/ም ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የመስክ ምልከታው ዓላማ ዩኒቨርሲቲው በተልዕኮው ልየታ መሠረት የ2016 ዓ/ም የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች በተገቢው እየተከናወኑ መሆናቸውን፣ የአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር  ያለበት ደረጃ፣ የ2015 ዓ/ም የተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተና ውጤት እና የ2016 ዓ/ም ቅድመ ዝግጅት፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሠሩ ያሉ ተግባራትንና ሌሎችን ተያያዥ ጉዳዮች ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ካሉ ዋና ተግባራት መካከል የሪፌራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ፣ የእንሰት ፕሮጀክት፣ የግብርና ምርትና የእንስሳት ሀብት፣ የተማሪዎች የመኝታና የምግብ አገልግሎት የመሳሳሉትን ተመልክተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከዩኒቨርሲቲው ተማሪ ተወካዮች የመውጫ ፈተና ዝግጅት፣ የተማሪ ቅበላ ቁጥር ማነስ፣ የምግብ፣ የጤና፣ የመኝታና የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ የወጪ መጋራት ክፍያ ሁኔታ፣ የመዝናኛ ቦታዎች ማነስ፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ ለተቋሙ የሚመደበው በጀት እጥረትና እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ፣  በመማር ማስተማር ላይ የአንዳንድ መምህራን የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ፣ የተግባር ትምህርት አሰጣጥ ማነስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በማጠቃለያ ሃሳባቸው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ የሚገኘው የጥናትና ምርምር ሥራዎች በተለይ የማዕድን ሀብት የአለኝታ ጥናት፣ በእንሰት ምርምር የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር የሴቶችን የሥራ ጫና፣ የጉልበትና የጊዜ እንዲሁም የምርት ብክነት መቀነስ፣ በ2015 ዓ/ም የመውጫ ፈተና 78 በመቶ ተመራቂ ተማሪዎችን ማሳለፍ፣ ሠላማዊ መማር ማስተማርን ማስቀጠል፣ የአመራሮች ተናቦ መሥራትና ሌሎችም በጥንካሬ የሚያዙና በተሻለ ሁኔታ ሊቀጥሉ የሚገቡ ናቸው፡፡

ሰብሳቢው በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ዕቅድ ውስጥ በትኩረት ተይዘው ያሉ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ካሳሰቧቸው ተግባራት መካከል የትምህርት ጥራት፣ የውኃና ግብርና ሳይንስ ዘርፎችን ልማታዊ ማድረግ፣ የ2016 ዓ/ም የመውጫ ፈተና ዝግጅት ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ ቤተ-ሙከራዎችን ማዘመን፣ የተማሪዎች መኝታ፣ መጸዳጃ ቤት፣ መመገቢያ፣ መማሪያና ማንበቢያ ቦታዎችን ምቹና ማራኪ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት