Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ፣ ነጭ ሳር፣ ኩልፎና ዓባያ ካምፓሶች ለሚገኙ የመጀመሪያ ዓመት ፍሬሽ ማን ኮርስ የጨረሱ ተማሪዎች በፋከልቲና ዲፓርትመንት መረጣ ዙሪያ ከጥር 09-10/2016 ዓ/ም ገለጻ ተደርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም የምኅንድስና ዘርፎች እርስ በእርስ እንደሚመጋገቡና ሁለቱ ኢንስቲትዩቶች በጋራ እንደሚሠሩ ገልጸው ተማሪዎች ያሉ ፕሮግራሞችንና የወደፊት ዕድሎችን አመዛዝነው በጥንቃቄ እንዲመርጡ አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለሀገራችን በርካታ ምሁራንና ባለውለታዎችን ያፈራና ጥሩ ስም ያለው በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው መማር በራሱ ተመራጭ ያደርጋችኋል ብለዋል፡፡ በመረጡት መስክ መሰማራት ውጤታማ ለመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት ዶ/ር ሙሉነህ በትምህርት መስክ ምርጫ ላይ የሀገሪቱን ፍላጎት፣ የመንግሥትን ፖሊሲና ዓለም አቀፍ ሁኔታን መሠረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፊዚዮሎጂ ት/ክፍል መምህርና የጋራ ኮርሶች አስተባባሪ ረ/ፕ እያዩ ግርማ በኮሌጁ የዲፓርትመንት ምርጫ በሁለት ዙር እንደሚካሄድ ጠቁመው ምርጫዎቹ በመጀመሪያው ሴሚስቴር መጨረሻ ያለውን ውጤት መሠረት በማድረግና በአንደኛ ዓመት መጨረሻ የሁለቱን ሴሚስቴሮች አጠቃላይ ውጤት መሠረት በማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

እንደ ረ/ፕ እያዩ ከዚህ ቀደም ለዲፓርትመንት መረጣ ይሰጥ የነበረው ፈተና በዚህ ዓመት የሌለ ሲሆን ለዲፓርትመንት ምርጫ 70 ከመቶ የመጀመሪያ ዓመት የፍሬሽ ማን ኮርስ የሁለቱ ሴሚስቴር ውጤት (GPA) እና 30 ከመቶ የ12 ክፍል ውጤታቸው ይያዛል፡፡ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ዘርፍ ያሉ የትምህርት ፕሮግራሞች ለሀገር አስፈላጊ በመሆናቸው ተማሪዎች የትኛውንም ዘርፍ ቢመርጡ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ያሉት አስተባባሪው በየዘርፉ ውጤታማ ለመሆን የግል ጥረትና ትጋት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ አምሳሉ ጣሰው በኮሌጁ ሰባት ዲፓርትመንቶችና 13 የትምህርት ፕሮግራሞች እንዳሉ ገልጸው ተማሪዎች የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ትምህርቶችን ከታችኛው ደረጃ ጀምረው እየተማሩ የመጡ በመሆኑ ምርጫቸው ቢያደርጉ ውጤታማ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ም/ዲን ዶ/ር ዮሐንስ ማሬ በበኩላቸው በኮሌጁ ስድስት ዲፓርትመንቶችና 11 የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ስለእያንዳንዱ የትምህርት ፕሮግራም በቂ ዕውቀት ኖሯቸውና ዝንባሌያቸውን ከግምት በማስገባት ምርጫውን እንዲያከናውኑ ዲኑ አሳስበዋል፡፡

ተማሪ ሔዋን አበበ በሰጠችው አስተያየት ገለጻው ስለምንመርጠው የትምህርት መስክና ወደፊት ስለሚኖረው የሥራ ዕድል በሚገባ ያብራራ በመሆኑ አመዛዝነን እንደየዝንባሌያችን ለመምረጥ ይረዳናል ብላለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት