Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በኢኮኖሚክስ ት/ክፍል በ‹‹Development Economics›› ትምህርት ፕሮግራም የ3 ዲግሪ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው ዕጩ ዶ/ር ሰሎሞን ከበደ የካቲት 01/2016 ዓ/ም የምርምር ሥራውን የውጪና የውስጥ ገምጋሚዎች እንዲሁም አማካሪዎች በተገኙበት አቅርቧል፡፡ የመመረቂያ ጽሑፉም አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ዕጩ ዶ/ር ሰለሞን ከበደ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እና ሁለተኛ ዲግሪውን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ‹‹Development Economics›› አግኝቷል፡፡ ዕጩ ዶ/ር ሰሎሞን ከበደ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ‹‹Development Economics›› የ3 ዲግሪ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየ ሲሆን የመመረቂያ ጽሑፉን ‹‹The Link Among Foreign Exchange Reserve, Foreign Public Debt, Foreign Direct Investment and Structural Transformation: Experiences from Sub-Saharan Africa, and East Asian and the Pacific Regions›› በሚል ርእስ አከናውኗል፡፡

ዕጩ ዶ/ር ሰሎሞን እንደገለጸው ጥናቱ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ የገንዘብ ምንጮች፣ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰትና ብድር የመሳሰሉት ኢኮኖሚውን ከማሻጋገር አንጻር ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ምን ዓይነት ሚና እንዳላቸው እና እያስከተሉ ያሉትን ውጤት ያሳያል፡፡ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባቸው ምርቶች እያመዘኑ መምጣት፣ የአስተዳደር ሥርዓቱ ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ መቀየር አለመቻሉ እና በብድር የሚገባው ገንዘብ ምንም ዓይነት ለውጥ እያመጣ አለመሆኑ በጥናቱ መመልከቱን ዕጩ ዶ/ር ሰሎሞን ተናግሯል፡፡ በመሆኑም የተቋማት ጥራት ላይ በስድስት ምክንያቶች ላይ ካልተሠራ ከውጭ የሚመጣው ዕዳ ለውጥ እንደማያመጣ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የአስተዳደር ችግሮች በመኖራቸው  ኢኮኖሚው ከግብርና መር ወደ ኢንደስትሪ ሊሸጋገር እንዳልቻለ አመላክቷል፡፡

የአስተዳደር ሥርዓቱን በደንብ መቃኘት፣ የውጭ ገንዘብ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ሀገር ውስጥ ያሉ አማራጮችን መጠቀም፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማሳደግ፣ ቦንድ በመሸጥ የሀገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮች ላይ በትኩረት መሥራት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ስላለ መንግሥት የውጭ ዕዳዎችን መቀነስና የሀገር ውስጥ ምርቶችን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪዎችን ማሳደግ እንዲሁም ከዚህ በፊት የነበሩ ዕዳዎችን በመመለስ ዕዳን መቀነስን በጥናቱ ለፖሊሲ ግብዓት ማቅረቡን ዕጩ ዶ/ር ሰሎሞን ተናግሯል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕ የሆኑት የውጭ ገምጋሚ ዶ/ር ወንድይፍራው ሙሉጌታ በጥናቱ የተቋማት ጥራትን ማሻሻል፣ የውጭ ጫናዎችን መቀነስና የተበደርነውን ለልማት ማዋል እንደሚገባ እንደተመላከተ ገልጸው ይህን የማናደርግ ከሆነ ያለብን የማክሮ ኢኮኖሚክስ ስብራቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ ብለዋል፡፡ አክለውም ሀገሪቱ አሁን ላለችበት የኢኮኖሚ ችግር በጥናቱ መፍትሔ አመላካች ሃሳብ እንደቀረበ ተናግረዋል፡፡

የውስጥ ገምጋሚ የሆኑት የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ ምርምሩ ለሀገሪቱ አስፈላጊና ወቅቱን የጠበቀ ግብዓት መሆኑን ገልጸው በተሰጡ አስተያየቶች እንዲዳብር እንዲሁም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ምርምሮችን ማካሄድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት