Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት መምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች በአዕምሮ ውቅር ዙሪያ ከየካቲት 4-6/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ መሰል ሥልጠናዎች ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ሚና ያላቸው በመሆኑ በጋራ የተማሪዎችን አዕምሮ ለመቅረጽ እና የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡  ስብዕናው የተሟላ፣ በዕውቀት የበለጸገና ጤናማ የአዕምሮ ውቅር ያለው ዜጋ ማፍራት አሁን ላይ ወሳኝ በመሆኑ መሰል የስብዕና ግንባታ ሥልጠናዎች ለተለያዩ ባለሙያዎች መድረስ እንዳለባቸውም ም/ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በሥልጠናው ተሳታፊዎች ላይ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ውጤታማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሥልጠናው የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው የት/ቤቱ ሠራተኞች መልካም ስብዕና እንዲኖራቸው በማድረግ በሂደት በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ የራሱን አዎንታዊ ሚና የሚጫወት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና አሠልጣኝ አቶ መርክነህ መኩሪያ በበኩላቸው ሥልጠናው ስብዕና ግንባታ ላይ የሚያተኩር ሲሆን እንደ ተቋም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና ለውጥ በማምጣት የተሻለ ትውልድ ለመቅረጽ ተዘጋጅቷል፡፡ ሠልጣኞች መምህራን እንደ መሆናቸው በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በተቋሙ በምግባር የታነጸ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል መ/ር ፍቃደ ወ/ሰንበት ሥልጠናው የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ራሳችንን እንድናይና በተቋሙ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንድናደርግ ያስቻለ ነው፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው ከሥራ ባለደረቦቻችንም ጋር ሆነ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር በጥሩ መግባባት የተሻለ አገልጋይና ሠራተኛ እንድንሆን ያገዘ ነው ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት