Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም ተጀምረው በተያዘላቸው ጊዜና በጀት መሠረት ባልተጠናቀቁ የምርምር ሥራዎች ላይ የካቲት 14/2016 ዓ/ም ዓመታዊ ግምገማ አካሂዷል፡፡  ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር አንለይ ብርሃኑ እንደገለጹት ግምገማው በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ዓላማውም ሂደቶችን በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን በመውሰድና ለሌሎች በማካፈል ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው እንዲማሩበትና የሚነሱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ ወደኋላ የቀሩ የምርምር ሥራዎች እንዲጠናቀቁ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

ዲኑ እንደ ትምህርት ቤት የትብብር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በብዛት ለሚሠሩ ተመራማሪዎች ቅድሚያ በመስጠት የሚያበረታታ አሠርር የተዘረጋ መሆኑን ገልጸው አነስተኛ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት በመቅረፍ እንዲሁም የተበጀተውን ገንዘብ ለተፈለገው ዓላማ በማዋል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራውን በትኩረትና በጥራት አጠናቀው ወደሚፈለገው ደረጃ እንዲያደርሱ አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ተመራማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው መደበኛ በጀት ይልቅ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ለመፍጠር በሚያስችሉ ሌሎች የትብብር ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንክረው እንዲሠሩ መክረው በዘርፉ ጅምር ሥራዎች መኖራቸውንም መ/ር አንለይ ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል በቀጣይ የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ተመሳሳይነት ያላቸው ምርምሮችን በማጣመር ግራንድ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶች የሚሠሩበት መንገድ ይመቻቻል ብለዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ቤታ ጻማቶ በበኩላቸው እየተከናወኑ ካሉ 22 ምርምሮች ሦስቱ  በጣም ጥሩ፣ ሦስቱ ጥሩ እንዲሁም አሥራ አንዱ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ሲሆኑ የተቀሩት አምስቱ በጣም ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ መማር ማስተማሩ ሁሉ ለምርምር ሥራ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል ያሉት ኃላፊው ምርምሮች በወቅቱና በጥራት ካልተሠሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በጀት የማስመለስ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል፡፡ በቀጣይ የተጀመሩ ምርምሮችን በመናበብና በመደጋገፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩና እንዲጠናቀቁ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተመራማሪዎች በሰጡት አስተያየት የተጠናቀቁ ምርምሮች የምርምር ሕጉን ጠብቀው ለመሥራት በሚደረገው ጥረት እና ባለው የበጀት ችግር ሊዘገዩ እንደሚችሉ እንዲሁም ምርምሩ መጠናቀቁ ላይ ብቻ ሳይሆን ጥራቱና ወደ መሬት ወርዶ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈታ መሆኑ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም የሚሠሩ ሰዎችን በጥራትና በመጠን በመለየት ተገቢውን ድጋፍና ዕውቅና በመስጠት ማበረታታት እንዲሁም በማይሠሩት ላይ ተገቢ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረው ጥራታቸውን ጠብቀው የተጠናቀቁ የምርምር ሥራዎች መታተም ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ እንደጸደቀ በጀት ቢለቀቅና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የበጀት ድጋፍ ተደርጎላቸው መጠናቀቅ እንዲችሉ ቢደረግ የሚል አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

በግምገማው ሂደት ተመራማሪዎች እየሠሯቸው ያሉ የምርምር ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ካቀረቡት ገለጻ ማስተዋል እንደተቻለው ከተወሰኑ የትብብርና አነስተኛ ፕሮጀክቶች ውጪ በአመዛኙ በተመደበው በጀት ልክ ሥራዎች ያልተሠሩ መሆኑ፣ እየተሠሩ ያሉት ምርምሮች የበጀት ችግር የገጠማቸው መሆኑና በቡድን የሚሠሩ ምርምሮች ከፍተኛ መጓተት የገጠማቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት