Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 53 ወንድ እና 17 ሴት በአጠቃላይ 70 የሕክምና ዶክተሮችን ለ9 ጊዜ የካቲት 16/2016 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ በመርሃ ግብሩ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይመረቁ የቆዩ ሦስት የ3 ዲግሪ፣ 237 የ2 ዲግሪ እና 509 የመጀመሪያ ዲግሪ በድምሩ 749 ተማሪዎችም ተመርቀዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 33ቱ ዩኒቨርሲቲው ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ በአደራ ተቀብሎ ያስተማራቸው ናቸው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከ79 ሺህ በላይ ምሩቃንን ለሀገር ማበርከቱን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው ሕክምና ት/ቤት ከተመሠረተበት 2001 ዓ/ም ጀምሮ የዛሬ ምሩቃንን ጨምሮ 755 የሕክምና ዶክተሮችን ማፍራቱን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ የዘንድሮ የሕክምና ተመራቂ ዶክተሮች ሀገር አቀፉን የመውጫ ፈተና ሙሉ በሙሉ በማለፋቸው የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል፡፡

የሕክምና ት/ቤቱ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታልን ለተግባር ልምምድ ሲጠቀምበት መቆየቱን ያስታወሱት ፕሬዝደንቱ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል በቅርቡ በከፊል ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ሆስፒታሉን በሕክምና ቁሳቁሶች ለማደራጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተውን ሂዩማን ብሪጅ/HUMAN BRiDGE/ የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅትና የድርጅቱን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በዩኒቨርሲቲው ስም አመስግነዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የቀድሞ አማካሪና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል ለምሩቃን ባስተላለፉት ቁልፍ መልእክት የሕክምናውን ዘርፍ ለማሻሻል እንደ ሀገር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እያሳዩ ቢሆንም ወጥታችሁ የምታገለግሉት አብዛኛው ኅብረተሰብ በኢኮኖሚ አቅሙ ደካማ፣ በተለያዩ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚጠቃ እንዲሁም እናቶችና ሕፃናት በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት ሞት ተጋላጭ የሆኑበት በመሆኑ ከወዲሁ የሙያ ፍቅርና ፅኑ አቋምን መያዝ ይገባችኋል ብለዋል፡፡ የሕክምና ሥራ በየጊዜው የሚዘምንና የሚራቀቅ ብሎም የቡድን ሥራን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ራስን በዕውቀት ማሳደግና ለሌሎችም ማጋራት እንዲሁም እርዳታን ፈልጎ የሚመጣውን ኅብረተሰብ በመፈቃቀርና በመተባበር በቅንነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

ከተመራቂ የሕክምና ዶክተሮች መካከል ዶ/ር ብሩክ ታረቀኝ 3.91፣ ዶ/ር ዮሐንስ ስምዖን 3.83 እና ዶ/ር ፍቅረአብ ከፍአለ 3.73 በማምጣት የተሸለሙ ሲሆን ዶ/ር ቅድስት አምታታው 3.34 በሆነ ነጥብ ከሴቶች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ልዩ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ ከአጠቃላይ ምሩቃን ከፍተኛ ውጤት ያለው ዶ/ር ብሩክ ታረቀኝ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

በመርሃ ግብሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል 600 የሕክምና አልጋዎችን ጨምሮ ከ250 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶችን እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የ‹‹HUMAN BRiDGE›› ግብረ ሠናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር አዳሙ አንለይ ዩኒቨርሲቲው የዕውቅና ክሪስታል አዋርድ፣ ምስክር ወረቀትና የምስጋና ስጦታ አበርክቷል፡፡

የሬጂስትራርና አሉምናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ የምሩቃንን አጠቃላይ መረጃ በመስጠት ለምርቃት ያቀረቡ ሲሆን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ምሩቃንን አስመርቀዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት