Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹SNV-SEFFA›› ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ‹‹Sustainable Energy for Smallholder Farmers›› በሚል ርእስ ከአርባ ምንጭ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ከመጡ ተመራማሪዎች ጋር የካቲት 26/2016 ዓ/ም ወርከሾፕ አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የ‹‹SNV›› ኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊና የ‹‹SEFFA›› ፕሮጀክት አስተባበሪ ወ/ሮ ሕይወቴ ተሾመ ወርክሾፑ በዋናነት ለአርሶ አደሩ ጥቅም ይሰጣሉ ተብለው የታመኑባቸውን ቴክኖሎጂዎች ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ ቅድመ መረጃ ለማግኘት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪዋ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር በተደረገው ስምምነት ተመራማሪዎች በየአካባቢያቸው የሚገኙ ምርቶችን ያማከለ ጥናት በማጥናት ከአርሶ አደሩ በተገኘው ምላሽ ዙሪያ ውይይት ሲደረግ የተሠሩ ሥራዎች ተመሳሳይ ጥሩ ውጤት ያሳዩ በመሆኑ በቀጣይ በተሻለ መልኩ ለማስኬድ ወርክሾፑ መስመር የሚያስይዝ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካልና ኮምፕዩተር ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና የ‹‹SEFFA›› ፕሮጀክት ወርክሾፕ አስተባባሪ መ/ር ፍሥሃ ከድር እንደገለጹት በፀሐይ ኃይል የማድረቅ ቴክኖሎጂን /Solar Dryer Technology and Application/ በመጠቀም አትክልትና ፍራፍሬን ማድረቅ አርሶ አደሩ ከማምረት ባለፈ ባመረተው ምርት በአግባቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚረዳውና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው፡፡ ወርክሾፑ አራቱን ዩኒቨርሲቲዎች በማሳተፍ የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም አትክልትና ፍራፍሬን ማድረቅን በተመለከተ የተሠራውን ሥራና የተገኘውን ውጤት የሚገመግም መሆኑን መ/ር ፍሥሃ ተናግረዋል፡፡ ሙዝን አድርቆ ለመጠቀም የተሠራውን መነሻ ሥራ ለአብነት የጠቀሱት መምህር ፍሥሃ ምርምሩን አርሶ አደሩ መጠቀም መፈለጉንና በስፋት መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲሁም የሙዝ ዱቄትን እንደማንኛውም የእህል ዱቄት መጠቀም የሚችልበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚቻልና ከሙዝ ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢነርጂ ማዕከል የመጡት መምህር እሸቱ ጌታሁን እንደገለጹት በባሕር ዳር ሰፊ የበርበሬ ምርት በመኖሩ የምርት ብክነትና የጥራት መቀነስን ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም እየተሠራ ነው፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ታረቀኝ ሊሞሬ በበኩላቸው በርበሬና ቲማቲምን በፀሐይ ኃይል ማድረቅ ላይ ምርምር መሥራታቸውን ገልጸው በልማድ በፀሐይ ከማድረቅ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ማድረቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማድረቅ፣ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅና በዝናብ ወቅት የሚከሰተውን የምረት ብክነት ለመቀነስ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ  የምግብ ሳይንስ ቴክኖሎጂ መምህር ረ/ፕ ይስሃቅ ወርቁ በተመሳሳይ በርበሬና ቲማቲምን በፀሐይ ኃይል ማድረቅ ላይ ምርምር መሥራታቸውና የቲማቲምን ክንውን ለማወቅ ካሮትን አስቀድመው በመጠቀም ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት