Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የአስተዳደር ዘርፍ ኃላፊዎች በአእምሮ ውቅር ዙሪያ ከመጋቢት 18-20/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹እኔ ማን ነኝ? ሕይወት ምንድን ነው? ለምን ተፈጠርኩ? ራእይን እንዴት እውን እናደርጋለን? የልማዶች ኃይል፣ የሕይወት ቁልፎች፣ አስተሳሰብና አመለካከት፣ ለውጥና የሰብእና ግንባታ፣ የሰብእና መለኪያና የሰብእና መዛባት ዓይነቶች›› የሚሉ ርእሰ ጉዳዮች በሥልጠናው ተዳስሰዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተካነ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈታ የሚችል ዜጋ የመፍጠር ራእዩን በማሳካት ሂደት ውስጥ የአእምሮ ልዕልናን መገንባት ያስፈልገዋል፡፡ በመሆኑም ከመማር ማስተማር ተግባር ጎን ለጎን ሰብእናው የተሟላ፣ በዕውቀት የበለጸገና ጤናማ የአእምሮ ውቅር ያለው ዜጋ ለማፍራት መሰል ሥልጠናዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ የአእምሮ ዝግጅት፣ የሥራ ተነሳሽነትና የባለቤትነት ስሜትን ለማዳበር የሰብእና ግንባታ ሥልጠናዎች ለተለያዩ ባለሙያዎች መድረስ አለባቸው ያሉት ዲኑ በአስተዳደር ዘርፍ ያሉ ሠራተኞችን አእምሮ ለመቅረጽ እና የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና አሠልጣኝ አቶ መርክነህ መኩሪያ በበኩላቸው ለውጥ በማምጣት የተሻለ ትውልድ ለመቅረጽ ራስን ማወቅ ስለሚያስፈልግና እንደ ተቋም አንዳንድ ክፍተቶችን ለመሙላት ሥልጠናው የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞች በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በተቋሙ በምግባር የታነጸ ተተኪ ትውልድ ማፍራት ብሎም በሀገር ደረጃ በአስተሳሰብና በአመለካከት የተለወጠ ማኅበረሰብ ማብቃት አለባቸውም ብለዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ማኔጂንግ ዳይ/ጽ/ቤት ተወካይና የሰው ሀብት ቡድን መሪ ወ/ሮ እሌኒ መኩሪያ እንደገለጹት በአዲስ ማንነት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ በመፍጠር እንደ ተቋም በሥራ ቦታ ላይ የሚታዩ የተለያዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የሰብእና ግንባታ ሥልጠና አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ሥልጠናውን የወሰዱ የቢሮ ኃላፊዎች ራሳቸውን በመቀየር ሌሎች በሥራቸው ያሉ ባለሙያዎችን መቀየር እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች ራስን ለማየት፣ ለማወቅና ፈልጎ ለማግኘት ሥልጠናው ትልቅ መስተዋት ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በሰው ሕይወት ላይ የጊዜን ጠቀሜታና በአግባቡ እንዴት መያዝ እንደሚገባ እንዲሁም ሰው ከውጪ ግፊት ይልቅ የውስጡን ማንነት ቢታዘዝ ስኬታማ እንደሚሆን ተረድተናልም ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት