Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እና የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የሦስትዮሽ መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በስምምነቱ መሠረት ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ያስፈልጋሉ የሚባሉ ትብብሮችን በማቀድ በፍጥነት ወደ ተግባር እንገባለን ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ደመላሽ ወንድማገኘሁ በበኩላቸው በሦስትዮሽ ስምምነቱ መሠረት በዋናነት ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ሐይቅ ጥልቀት፣ ስፋትና አጠቃላይ የአካባቢውን ሁኔታ የማወቅ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኩል እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የኢትዮጵያን ባሕር እሴት የሚያስጠብቅ ተቋም በመሆኑ ጥናቱን በጋራ ለመሥራት ተፈራርመናል ያሉት ዶ/ር ወንድማገኘሁ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የካርታ ሥራውን እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ ጥናቱ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ይጀመር እንጂ በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ የውኃ አካላት ላይ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ተወካይ ሬር አድሚራል ናስር አባዲጋ እንደገለጹት በሦስቱ ተቋማት የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ዓላማ የውኃ አካሎች መረጃ ልውውጥ፣ የውኃ አካላት ካርታ ኅትመት እና በጂኦስፓሻልና ሪሞት ሴንሲንግ መስክ እየተገነባ ያለውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አቅም ማጎልበት ነው፡፡

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተር አቶ በላቸው ፀሐይ በበኩላቸው የባሕር ኃይልን ለመገንባት መንግሥት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን አስታውሰው በተፈራረምንባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት