በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ‹‹የምሁራንና የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን!›› በሚል መሪ ቃል ግንቦት 24/2013 ዓ.ም ሀገራዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዕለቱ በ5 ምሁራን የውይይት መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደ ሲሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያው የተሳካ የውሃ ሙሌት እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ያለውን የግንባታ ሂደት እንዲሁም የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ጉዞ የሚያሳይ የፎቶ ዓውደ ርዕይም ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አለኝታ 223 ቢሊየን ሜ.ኩ ሲሆን 77 ቢሊየን ሜ.ኩ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ይፈሳል፡፡ በአጠቃላይ 49 ቢሊየን ሜ.ኩ 59 በመቶ ከተከዜ 11.2 በመቶ ቀጥታ ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ሱዳን በመፍሰስ ከደንደር ወንዝ ጋር በመቀላቀል ወደ ነጭ ዓባይ የሚገባ ሲሆን ባሮ በበኩሉ 13 ቢሊየን ሜ.ኩ ለዓባይ ወንዝ ይገብራል፡፡ የዓባይን ውሃ 86 በመቶ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ከ60-60.5 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አለመሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ስለሺ ኢትዮጵያ ከራሷ የሚፈልቀውን ሀብት አትጠቀም ማለት በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ስለሺ ማብራሪያ በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና ፍላጎት ለማጣጣም የግድቡ ግንባታ አስፈላጊ ነው፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በመስኖ፣ በማዕድንና በቱሪዝም ዘርፎች ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡ ከዚህም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ለማስተካከልና ድርቅን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሆን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በጎርፍ እንዳይጎዱም ይከላከላል፡፡ በመሆኑም ግድቡ ለፍፃሜ እንዲበቃና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ልዩነቶች ሳይበግሩን በአንድነት መቆም ይገባናል ብለዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብ/ም/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ከውይይት ባለፈ መሬት ላይ ሊወርዱ በሚችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህዳሴውን ግድብ እውን መሆን በ2014 ዓ.ም ዕቅዳቸው ውስጥ አካተው መሥራትና ሕዝባዊ ተሳትፎውም ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የግድቡ ሥራ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ ያለበትና የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የግድቡን ግንባታ ለማሳካት በልዩ ልዩ መንገድ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ተሳትፎው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

መድረኩ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እውን ለማድረግ ምሁራንንና ዜጎችን ለማነቃቃት የተዘጋጀ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ገልጸዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አህመድ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ኢትዮጵያና ቱርክ ተመሳሳይ የውሃ ፖለቲካ ችግር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ቱርክ በቅኝ ግዛት ወቅት በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች ላይ ሶሪያና ፈረንሳይ በፈረሙት ስምምነት ምክንያት ቱርክ በወንዞቹ ላይ ግድብ ለመሥራት ከዓለም ባንክ በኩል ችግር የገጠማት ሲሆን ኢትዮጵያም በ1929 ዓ.ም እና በ1959 ዓ.ም በሱዳንና በግብጽ በኩል የተፈረመ የቅኝ ግዛት ወቅት ስምምነት በመኖሩ የህዳሴውን ግድብ ለመሥራት ብድር ተከልክላለች፡፡

ከፕሮግራሙ ጋር በተያያዘ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም የክብርና ተጋባዥ እንግዶቹ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር 3ኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ችግኝ በመትከል አስጀምረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብ/ም/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ የጋሞና የጎፋ ዞኖች አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራን፣ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው የአማካሪ ም/ቤት ተወካዮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት