የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለአርባ ምንጭ ከተማ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በተለያዩ የሕግ ጉዳዮች ዙሪያ ከግንቦት 18-19/2013 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የሚታዩ የሕግ ክሂሎት ክፍተቶችን ለማሻሻል እየሠሩ መሆኑን ጠቁመው ሥልጠናው ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት የሚሠሩ የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች የሕግ ዕውቀታቸውን እንዲያሳድጉ ታልሞ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው በሰብአዊ መብቶች፣ በቤተሰብ፣ በውርስ፣ በንብረት፣ በሥነ-ሥርዓት እና ማስረጃ ሕጎች እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናት መብት ዙሪያ የተሰጠ መሆኑን የት/ቤቱ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ር ዳኛቸው ወርቁ ገልጸዋል፡፡ ለማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚቀርቡ ጉዳዮች በደቡብ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግሥት አዲስ በተቋቋመው አዋጅ መሠረት የተለዩ መሆናቸውን መ/ር ዳኛቸው ተናግረው ሥልጠናው ዳኞቹ የሥልጣን ወሰናቸውን ለይተው በመረዳት ማኅበረሰቡን በተገቢው ሁኔታ ለማገልገል የሚረዳቸው ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስለተለያዩ የሕግ ጭብጦች መገንዘባቸውንና ከዚህ ቀደም ክፍተቶች ያሉባቸው አሠራሮችን በማስቀረት በዕውቀት እንዲያገለግሉ አቅም የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል

በሥልጠናው የማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የመዝገብ ቤት ሠራተኞች፣ የጸጥታ አካላትና የቀበሌ አስተዳደሮች ተሳትፈውበታል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት