የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከምዕራብ ዓባያና ከአርባ ምንጭ ከተማ ለተወጣጡ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን ግንቦት 14/2013 ዓ/ም የተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ንባብ ክሂሎት ማሻሻያ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፊደላት፣ ድምጽና ስያሜያቸው እንዲሁም ተነባቢና አናባቢ ድምጾች በቃላት ውስጥ ሲገቡ የሚያመጡትን ለውጥ ለተማሪዎቹ የሚያስተምሩበት ስነ-ዘዴ በስፋት ተዳሷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ ኤርሚያስ በፈቃዱ እንደገለጹት የተማሪዎች የማንበብ ክሂሎት ከትምህርት ጥራት ጋር የሚያያዝና ችግሩ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለመፍትሔው የበኩሉን ለማበርከት ሥልጠናውን አዘጋጅቷል፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ መሐመድ ሹሬ በበኩላቸው መምህራኑ የሠለጠኑበትን ሥነ-ዘዴ በተግባር ላይ በማዋል በተማሪዎች ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አባተ አንጁሎ በሥልጠናው መምህራን ፊደላትን፣ ቃላትንና ዓረፍተ ነገሮችን ቀላልና ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ለተማሪዎች እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው ክሂሎት መጨበጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ዶ/ር መለሰ መንገሻ ሥልጠናው በቡድን የተሠራ የጥናትና ምርምር ውጤትን መሠረት አድርጎ መሰጠቱ መልካም መሆኑን ገልጸው የተማሪዎች የንባብ ክሂሎት እንደ ሀገር አሳሳቢ በመሆኑ ከታችኛው ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር መለሰ በሁለት ት/ቤቶች ላይ ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ተመርጠው ቢያንስ ለሁለት ወር ከመምህራን ጋር ክትትል እያደረጉ እንደሚሠሩና የተሻለ ውጤት ከታየባቸው ወደ ሌሎች ት/ቤቶች የሚስፋፋ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በክሂሎት ማነስ ምክንያት በተለምዶ እየሠሩ እንደነበርና በሥልጠናው ያገኙትን ክሂሎት በሥራ ላይ የሚያውሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ አመራሮች፣ ርዕሳነ መምህራንና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት