የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕ/ጽ/ቤት ‹‹International Water Management›› /IWMT/፣ ከዓለም አቀፍ ውሃ አመራር ተቋም እና ከ‹‹AGRUMIG›› ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በፍልሰት እና በግብርናና ገጠር ልማት መካካል ያለውን ቁርኝትና ግብርናው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ ሐምሌ 04/2013 ዓ/ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ጥናቱ ከገጠር ወደ ከተማ እንዲሁም ከሀገር ውጭ የሚደረገው የሰዎች ፍልሰት በገጠሩ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጫናና ተያያዥ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ለመለየትና በቀጣይም ፖሊሲ ለማውጣት የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን ለማዳበር የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ከዓለም አቀፍ ውሃ አመራር ተቋም የመጡት ዶ/ር መንግሥቱ ደሳለኝ የፍልሰትን አሉታዊና አዎንታዊ ተጽዕኖዎች ለማወቅ በተለያዩ አካባቢዎች ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው የውይይት መድረኩ ከሚመለከታቸው አካላት ለጥናቱ የሚያግዙና በቀጣይ ፖሊሲ ለመንደፍ የሚያስችሉ ሃሳቦችን ለማግኘት የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግሥት ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ስምሪትና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ በዛብህ እንደገለጹት በክልሉ ድህነትን ለማሸነፍ ሲባል ፍልሰት እየጨመረ የመጣ ሲሆን መንግሥት ሕገ-ወጥ ፍልሰትን የመከላከል ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሕጋዊ መንገድን የተከተለ ፍልሰት የቤተሰብ ኑሮን የሚያሻሽል፣ ምርታማነትን የሚያሳድግና በውጭ ምንዛሪ ሀገሪቷን የሚጠቅም መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ነገር ግን ሰፊ የእርሻ መሬት እያለን ወጣት አምራች ዜጋ የሚጠፋ ከሆነ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል የፍልሰት አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑ ላይ ሰፊ ጥናት እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት እና ከሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ት/ክፍል የተወጣጡ ምሁራን፣ ከጋሞ ዞን ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ፣ ከደቡብ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት፣ ከዓለም አቀፍ ውሃ ምርምር ተቋም፣ ከጋሞ ዞን የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ጽ/ቤት፣ ከጋሞ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ከስደት ተመላሽ ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት