የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል ከኢትዮጵያ ሥራ ፈጠራ ልማት ማዕከል ጋር በመተባበር በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህራን ከጥቅምት 29 -ኅዳር 4/2014 ዓ/ም የሥራ ፈጠራ ክሂሎት የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው በማስተማሪያ ሥነ-ዘዴ እንዲሁም በስኬታማ ሥራ ፈጣሪ ብቃትና ባህሪያት ላይ በመመርኮዝ ቢዝነስ ጀምሮ ማሳየትና መተግበር ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሥራ ፈጠራ ልማት ማዕከል ሀዋሳ ቅርንጫፍ የሥራ ፈጠራ ልማት አሠልጣኝና የቢዝነስ አማካሪ አቶ ፍሬው ዘውዴ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ በአካባቢው ያለውን ሀብት በመጠቀም ጠንካራና ሥራ መፍጠር የሚችል ዜጋን ማፍራት ሲሆን መምህራን የማስተማሪያ ዘዴያቸው አሳታፊ፣ ተግባር ተኮርና ውጤታማ እንዲሆንም ያግዛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ አበበ ዘየደ በበኩላቸው ሥልጠናው የሥራ ፈጠራ አመለካከታቸውን የሚቀይር፣ ብቃታቸውን የሚገመግሙበት እንዲሁም የጀመሩትን ቢዝነስ ለመቀጠል የሚያስችል ሞራልና መነሳሳት የሚያገኙበት ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኝ ዶ/ር መስፍን መንዛ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም የአሠልጣኞች ሥልጠናው ለውስን መምህራን ብቻ በመሰጠቱ የተለያዩ ሥልጠናዎች ሲዘጋጁ የአሠልጣኝ እጥረት ያጋጥም እንደነበር አስታውሰው በዚህ ዙር በርካታ መምህራንን ያሳተፈ በመሆኑ እንደ ኮሌጅ ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአካውንቲንግና ፋይናንስ ት/ክፍል ሠልጣኝ የሆኑት መምህር ርሆቦት ታሉ በበኩላቸው ሥልጠናው ንድፈ-ሃሳብን ከተግባር ያጣመረ በመሆኑ ተማሪዎች ሳይሰለቹ እንዲማሩ ማራኪ የትምህርት አቀራረብ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በመዝጊያ ንግግራቸው ማዕከሉ ከዳይሬክቶሬቱ ጋር በቅንጅት የሚሠራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ሥልጠናውን በየኮሌጁ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት