ዓለም አቀፍ የነጭ ሪባን ቀን ‹‹በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ጥቃቶችን በመከላከልና በማስቆም አጋርነታችንን እናሳይ!›› በሚል መሪ ቃል ሳውላ ካምፓስን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲው ሁሉም ካምፓሶች ከኅዳር 16/2014 ዓ/ም ጀምሮ ተከብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ በኢትዮጵያ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን በዋናነት ወንዶች በሴቶችና ሕፃናት ላይ ጥቃት ላለመፈጸም ወይም ሲፈጸም ዳር ቆሞ ላለማየት፣ ላለመተባበርና ተፈጥሮ ቢገኝ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ከሌሎች ወገኖች ጋር በመሆን ለመታገል ቃል የሚገቡበት እና አጋርነታቸውን የሚገልጹበት ቀን መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ሴ/ሕ/ወ/ጉ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዓሉ ለሴት ተማሪዎች ምቹ የሆነ የትምህርት ተቋም መፈጠሩንና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥራዎች መተግበራቸውን የምንፈትሽበት ብሎም ክፍተት በሚስተዋልባቸው ዘርፎች ላይ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተን ለመሥራት ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴ/ሕ/ወ/ጉ/ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ እንደገለጹት ጾታዊ ጥቃት ጾታን መሠረት በማድረግ በግለሰብ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳትን የሚያስከትል ሕገ ወጥ ተግባር ነው፡፡ ጥቃቱን ለማስቆም የቅድመ መከላከልን ሥራዎችን ከመሥራት፣ ጥቃት ተፈጽሞ ሲገኝ ተገቢ፣ አፋጣኝና አስተማሪ ቅጣቶችንና ምላሾችን ከመስጠት፣ ተጠቂዎች ከሚደርስባቸው አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት እንዲያገግሙ የሚያግዝ ጠንካራ ሥርዓት ከመፍጠር አንጻር የሁሉም አካላት ሚና ሊጎለብት ይገባዋል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ማኅበረሰቡም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት በእኔነት መንፈስ ጥቃትን መከላከል ተቀዳሚ ተግባራቸው ማድረግ፣ እርስ በርስ የመጠባበቅ ባህልን ማዳበርና የሌላውን ህመም እንደራስ አድርጎ መቀበልን መልመድ ተገቢ እንደሆነም አቶ ታደለ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ አብርሃም ክንፈ ባቀረቡት ሰነድ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የፍትህ አካላት ትልቅ ሚና መጫወት የሚገባቸው ሲሆን ጥቃቱን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓቱ ጥንካሬ ወሳኝነት አለው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የጾታዊ ትንኮሳ ምንነትና ዓይነቶች፣ የቤተሰብ ሕግ፣ የቅጥር ሕግ፣ የወንጀል ሕግ፣ የሴቶች እኩልነት መብት ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ስምምነት አንጻር፣ የጾታዊ እኩልነት መብት፣ ልዩ ዓለም አቀፍ የሴቶች ስምምነት፣ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነቶችን ለማስወገድ የወጣ ስምምነትና መሰል ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ከበዓሉ ታዳሚዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት