በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በተደረገ ሀገር አቀፍ የምግብ ፈጠራ ሥራዎች ውድድር 1ኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ውድድሩ ከኅዳር 29 - ታኅሣሥ 1/2014 ዓ/ም ከተካሄደው ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግብ ምርምር ኮንፍረንስ ጋር ተያይዞ የተደረገ ሲሆን በውድድሩ ከ11 ተቋማት የተወጣጡ የፈጠራ ሰዎች ተካፍለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በመወከል የተወዳደሩት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በውድደሩ ላይ በዋናነት የእንሰት ተክል ውጤቶችን በመጠቀም የሠሯቸውን የተለያዩ እሴት የተጨመረባቸው አዳዲስ የምግብ ዓይነቶች ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ከምግቦቹ መካከል ለነፍሰጡርና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ለታዳጊ ሕፃናት እንዲሆን ታስቦ የእንሰት አሚቾን ከሌሎች ተፈጥሯዊ የእህል ዝርያዎች ጋር በመቀመም የተዘጋጀ የምግብ ዓይነት ይገኝበታል፡፡ ምግቡ ለነፍሰጡርና አጥቢ እናቶች በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ካልሺየም፣ አይረን፣ ፎሊክ አሲድና ዚንክ የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ንጥረ ነገሮቹን ለማግኘት የሚሰጡ መድኃኒቶችን የሚያስቀርና በዋናነት በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ማነስን የሚከላከል መሆኑን ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

ሌላው ለውድድር የቀረበው የምግብ ዓይነት በተፈጥሮው የፕሮቲን መጠኑ አነስተኛ የሆነውን ቆጮ ከሞሪንጋ ጋር አብሮ በማብላላት ቆጮን በፕሮቲን የበለጸገ እንዲሆን ያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም ለኬክና መሰል የምግብ ዓይነቶች መሥሪያ የሚሆን ከእጅ ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ የተመረተ የቆጮና የቡላ ዱቄትም በውድድሩ ቀርቧል፡፡

በውድድሩ አሸናፊ በመሆናቸው በእጅጉ እንደተደሰቱ የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ ሽልማትና ዕውቅናው ለቀጣይ አዳዲስ ሥራዎች የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡ ከውድድሩ ባሻገር በፕሮግራሙ ተሳታፊ የነበሩ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ተቋማት አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምግቦቹ ሙሉ በመሉ ወደ ገበያ በሚገቡበት ሁኔታና ቀሪ የሙከራ ሥራዎች ላይ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጤና ሚኒስቴር የሰቆጣ ዲክላሬሽን አስተባባሪዎች የቀረቡት የምግብ ዓይነቶች የሕፃናት መቀንጨርን ከማስቀረት አንፃር ያላቸውን ሚና ተገንዘበው አብሮ ለመሥራት ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል፡፡

ዶ/ር አዲሱ ከዚህ በፊት ከእንሰት የአመራረትና የማብላላት ሂደት ጋር ተያይዞ በሠሯቸው የፈጠራ ሥራዎች በተለያየ ጊዜ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገር አቀፋዊ ሽልማቶችንና ዕውቅናዎችን ማግኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ፈጠራዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ ለማውረድ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየተሠራ ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት