የሀገር መከላከያ ሠራዊትን፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችንና የዘማች ቤተሰቦችን ለመደገፍ የ2ኛ ደረጃ መምህራንንና ተማሪዎችን በማሳተፍ የተጀመረው ሀገራዊ የድጋፍ ዘመቻ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር በዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ታኅሣሥ 01/2014 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ከኅዳር 27 - ታኅሣሥ 01/2014 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወነውን ዘመቻ ምክንያት በማድረግ የት/ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች ከጫኖ ቀበሌ ጀምሮ በአርባ ምንጭ ከተማ ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ የተለያዩ አልባሳት፣ የሴቶች ንፅሕና መጠበቂያ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ በርበሬና የመሳሰሉ ምግቦች እንዲሁም በጥሬ ገንዘብ 69,364 ብር መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና ፕሮግራሙ በሀገር ጉዳይ ያለንን አቋም በአንድነት በመቆም ማሳየት የሚያስችለን፣ እርስ በእርሳችን እንድንተዋወቅ የሚያደርገን እንዲሁም ተማሪዎቻችን ዕውቀትና ተነሳሽነታቸውን ለሀገር በሚጠቅም መልኩ እንዲጠቀሙ የረዳ ነው ብለዋል፡፡ የሀገር መከላከያንና መላውን የጸጥታ ኃይል ማጠናከር፣ በጦርነቱ የተጎዱትን ማቋቋምና ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ጦርነት ፍትሃዊነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለዓለም ሕዝብ ማሳወቅ የሚገባ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ይህ የመተባበር ስሜትና አንድነት በመማር ማስተማርም ሆነ በመልካም ሥነ-ምግባር ቀረጻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የት/ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የት/ቤቱ 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በመቀበልና ትምህርታቸውን በነጻነት ለመማር ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቆም አለባት በማለት ስላደረጉት አበርክቶ አመስግነዋል፡፡ የዛሬ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶች በመሆናቸው በትምህርታቸው ስኬታማ ለመሆን እርስ በእርሳችው መደጋገፍ፣ መረዳዳትና የመምህራንን ምክርና ትዕዛዝ መቀበል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

የት/ቤቱ የታሪክ መምህር አቶ አክሊሉ አይዛ ሕወሓትና ምዕራባውያን ጥቅማቸውን ያለ ከልካይ ለማስጠበቅ ጥቅሜን ያስከብርልኛል ያሏቸውን ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች ዋነኛ መሳሪያ አድርገው እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው በዚህም በተለይ ምዕራባውያን በተለያዩ ሀገራት ጣልቃ በመግባት መሪዎቻቸውን በኃይል ከሥልጣን በማንሳት በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘላቂ አለመረጋጋትና ጫና በመፍጠር ዜጎች የተወሳሰበ ሕይወት እንዲገፉ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ለውጭ ተፅዕኖ ሳትበገር ክብሯን አስጠብቃ የቆየችና ወደ ፊትም ሉዓላዊነቷን አስከብራ የምትኖር ሀገር እንደምትሆንም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የከተማዋ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የት/ቤቱ አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች በመርሃ-ግብሩ ታድመዋል፡፡ በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያም በድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴነት ተመድበው ሲያስተባብሩ ለቆዩ የት/ቤቱ መምህራን የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት