የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ አማርኛ ት/ክፍል ጋር በመተባበር ለአርባ ምንጭ ከተማ ማረሚያ ተቋም፣ ለጨንቻ ከተማ ወጣቶች ቤተ-መጻሕፍትና በጨንቻ ለሚገኘው ሆሎኦና ላካ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ታኅሣሥ 6/2014 ዓ.ም የመጻሕፍት ድጋፍ አድርጓል፡፡ መጻሕፍቱ በቁጥር 433 ሲሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የተለያዩ ጀግኖች ታሪክ፣ ልብወለዶች፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ፣ የቋንቋ እና የትምህርት ማጣቀሻዎችን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ ኤርሚያስ በፈቃዱ ድጋፉ የአንባቢውን ስብዕና በመገንባትና በዕውቀት በማነጽ ለሀገር ተቆርቋሪ ዜጋን ለማፍራት ያለመ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲና ማኅበረሰብ የማይነጣጠሉ እንዲሁም በመማር ማስተማር ሂደት የመጻሕፍት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሹሬ በበኩላቸው በሥራ ክፍሉ ለማኅበረሰቡ በርካታ ድጋፎች መደረጋቸውን አስታውሰው የመጻሕፍት ድጋፉ ትውልዱ የንባብ ባህሉን እንዲያዳብር ከማስቻል ባለፈ ሥነ-ምግባርን ለማነጽ ያግዛል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር ዓለሙ ኬንቶ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጉዳዮች ከተቋማቸው ጋር በቅንጅት ሲሠራ የቆየ ሲሆን የመጻሕፍት ድጋፉ ታራሚዎች በሥነ-ምግባር እንዲታነፁና በአመለካከት ራሳቸውን እንዲቀይሩ የሚያግዙ ናቸው፡፡

የጨንቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ጌታቸው በበኩላቸው መጻሕፍቱ ወጣቶችን አልባሌ ቦታዎች ከመዋል የሚታደጉና ራሳቸውን በዕውቀት የሚገነቡበት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ከማኅበረሰቡ ጋር ለመሥራት ባቀዷቸው ጉዳዮች ዩኒቨርሲቲው ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

የሆሎኦና ላካ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አክሊሉ አሌ እንደገለጹት ድጋፉ በቤተ-መጻሕፍቱ የሚስተዋለውን የመጻሕፍት እጥረት የሚቀንስና ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የማያገኙትን የእውቀት ክፍተት የሚሞላላቸው ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት