የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት እና ከጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ ጋር በመተባበር በፎረንሲክ ወንጀል ምርመራ ዘዴና ማስረጃ አያያዝ ዙሪያ ከጋሞ ዞን ለተወጣጡ 36 የፎረንሲክ ምርመራ ፖሊስ መኮንኖች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ለተወጣጡ የጥበቃ ሠራተኞች ከታኅሣሥ 7-9/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም የሥልጠናው ዓላማ በየወረዳው ያሉ ባለሙያዎች በፎረንሲክ ምርመራ ዙሪያ የነበረባቸውን የክሂሎት ክፍተት በመሙላት ግንዛቤያቸውን ማጎልበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ዳኛቸው ወርቁ በበኩላቸው ሥልጠናው ከሕግ አንጻር የፎረንሲክ ምርመራ ማስረጃዎች በፍርድ ቤቶች አግባብነትና ተቀባይነት የሚያገኙበትን ሁኔታና የፎረንሲክ ማስረጃዎች ራሳቸውን ችለው ብይን ለመስጠት ሚዛን የሚደፉ ወይም ደጋፊ ማስረጃዎች መሆናቸውን ለይተው ግንዛቤ እንዲጨብጡ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በኬሚስትሪ ት/ክፍል የፎረንሲክ ቶክሲኮሎጂ መምህርና አሠልጣኝ ኢዮብ ሙሉጌታ ፎረንሲክ ሳይንስ ሳይንሳዊ ዘዴን በመጠቀም ወንጀልን መመርመርና ለፍትሕ ማቅረብ መሆኑን ገልጸው የፎረንሲክ ሳይንቲስቱ ወንጀል በተፈጸመበት ሥፍራ ተገኝቶ ሳይንስን መሠረት ባደረገ እውቀት መረጃ መሰብሰብ፣ መረጃውን መጠበቅና ለፍትሕ አካል ማቅረብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በሀገራችንም ይሁን በዓለም ላይ የሚፈጸሙ ታላላቅና የረቀቁ ምሥጢራዊ ወንጀሎችን ለመዋጋት ዩኒቨርሲቲው ፕሮግራሙን ከፍቶ እየሠራ በመሆኑ ማኅበረሰቡ እንዲጠቀም አሳስበው የፖሊስ ተቋማትም መሰል ሥልጠናዎችን በመውሰድ በቀጣይ ወንጀልን ለመከላከል አብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡

የፎረንሲክ ማስረጃዎች ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ያላቸውን አስተዋፅዖ አስመልክተው ሥልጠና የሰጡት የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ጎድሴንድ ኮኖፋ ጥራት ያለውና ተአማኒ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት የፎረንሲክ ሳይንስ ምርመራ ጥበብና ማስረጃ አስፈላጊነት ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ የመጣበት ዋነኛው ምክንያት ከዐይን እማኝ ማስረጃ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ድክመቶች መኖራቸው ነው ብለዋል፡፡ የፎረንሲክ ማስረጃ በዐይን እማኝ ምስክርነት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

መ/ር ጎድሴንድ አንዳንድ ወንጀሎች ከአፈፃፀም ሁኔታቸው የተነሳ የዐይን እማኝ ማግኘት የማይቻልባቸው አጋጣሚዎች ሲከሰቱ በፎረንሲክ ሳይንስ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የማስረጃ ምንነት፣ ዓይነትና ዓላማ እንዲሁም የፎረንሲክ ሳይንስ ማስረጃ በኢትዮጵያ ሕግ ያለውን ተቀባይነት አስመልክቶ በሥልጠናው ተቃኝቷል፡፡

ሌላኛው አሠልጣኝ የፎረንሲክ ሳይንስ መምህር ዶ/ር ዲበሲስ ቦራ ሰዎች ወንጀልን ለመደበቅ ሲሉ እሳትን እንደሚያስነሱ ገልጸው አንድ የእሳት አደጋ ወንጀል መርማሪ ወንጀል የተፈፀመበት ቦታ ሲደርስ ወንጀሉ ሆን ተብሎ የተፈፀመ መሆኑንና አለመሆኑን፣ መነሻ ቦታውን እና ምክንያቱን መለየት እንዳለበትና በጥንቃቄ ናሙናዎችን ወስዶ በማሸግ ወደ ቤተ ሙከራ

ማድረስ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የእግር ዱካና የጣት አሻራ ወንጀሎችን አስመልክቶ የግለሰቡን ማንነት በቀላሉ እንዴት መለየት እንደሚቻልም በሥልጠናቸው ተካቷል፡፡

የፎረንሲክ ሳይንስ መምህር ዶ/ር አሊ ራዛ ጥያቄ ያለባቸው ሠነዶች የምርመራ ሂደትና አቀራረብ፣ ጥርጣሬ ያለባቸው ሠነዶች መረጃው ሳይጠፋና ባህሪውን ሳይቀይር መለየት እንዲሁም የወንጀል ድርጊት የተፈፀመበትን ቦታና ሁኔታ መለየት የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በስፋት በሥልጠናቸው ዳሰዋል፡፡

ሥልጠናው የነበረብንን የክሂሎት ክፍተት በመቅረፍ ወንጀለኛን በፍጥነት ለፍትሕ ማቅረብ እንድንችል ግንዛቤ ፈጥሮልናል ያሉት የጋሞ ዞን ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ም/ኢንስፔክተር ስንዱ አየለ በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀትና የምርመራ መሳሪያውን በመጠቀም የወንጀል ውጤቶችን በአጭር ጊዜ ለማግኘት እንሠራለን ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ሥልጠናውን እንዲያገኙ በማድረጉም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመዝጊያ ንግግራቸው ሠልጣኞች ለከተማችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም መሆን ትልቁን ድርሻ የምትወጡ እንደመሆናችሁ መጠን ከሥልጠናው ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ በቀጣይም ጠንክራችሁ ዩኒቨርሲቲውንና አካባቢውን ልትጠብቁ ይገባል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት