በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኤሌትሪካል እና ኮምፕዩተር ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር፣ ተመራማሪና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አንቺት ቢጀልዋን (Dr Anchit Bijalwan) ‹‹Network Forensics፡ Privacy and Security›› በሚል ርዕስ 2ኛ መጽሐፋቸውን አሳትመዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በፋከልቲው ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አንቺት ከዚህ ቀደም ‹‹Advance of Java Programming›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳተመዋል፡፡ በ‹‹Privacy and Security›› የትምህርት ዘርፍ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠኑ ሲሆን ከ40 በላይ የምርምር ሥራዎቻቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ ገምጋሚ በመሆንም እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ከመጽሐፉ ኅትመት ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር አንቺት በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ለተለያዩ ዓላማዎች በይነመረብን የሚጠቀሙ ሰዎችና ተቋማት ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ከሳይበር ደኅንነት አሳሳቢነትና በዘርፉ የሚስተዋለውን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት እንዲሁም ለዘርፉ ዕድገት የራሳቸውን አዎንታዊ ሚና ለመወጣት በማለም መጽሐፉን ለማዘጋጀት እንደተነሳሱ ገልጸዋል፡፡

መጽሐፉ በ12 ምዕራፎች የተከፈለና 3 ዓበይት ጉዳዮች በስፋት የተዳሰሱበት ሲሆን መጽሐፉን ለማዘጋጀት 2 ዓመታት እንደፈጀባቸው ዶ/ር አንቺት ተናግረዋል፡፡ የመጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍል ከኔትወርክ ፎረንሲክስ ጽንሰ ሃሳብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በስፋት የተተነተኑበት ሲሆን 2ኛው ክፍል የኔትወርክ ፎረንሲክስ ሥራን ለማከናወን የሚረዱ ዘዴዎችንና ቴክኒኮችን ይዟል፡፡የሳይበር ጥቃቶችን መለየትና መከላከል እንዲሁም ፈፃሚዎችን ማወቅ በኔትወርክ ፎረንሲክስ ሥራ ትልቁ አካል በመሆኑ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን የሚያስችሉ የምርመራ፣ ጥፋተኞችን የማግኛ ዘዴዎችና ሌሎች ጉዳዮች የተተነተኑበት 3ኛው የመጽሐፉ ትኩረት መሆኑንም ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡

ኔትወርክ ፎረንሲክስ የኮምፕዩተር ኔትወርክ ትራፊክን ለመረጃ አሰባሰብ፣ ሕጋዊ ማስረጃ ለማግኘት የሚደረግ ክትትልና ትንተናን የሚመለከት የዲጂታል ፎረንሲክስ ንዑስ ቅርንጫፍ ነው ያሉት ዶ/ር አንቺት መጽሐፉ ከኮምፕዩተር ኔትወርክ ጋር የተያያዘ ትምህርት ለሚያጠኑ የቅድመና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም ለተመራማሪዎች ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል። መጽሐፉን ማንኛውም ሰው ገዝቶ ቢያነበው ከሳይበር ደኅንነት ጋር ተያይዞ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ዕውቀቶች ጋር ይተዋወቃል ያሉት ጸሐፊው ከዚህም ባሻገር ከሳይበር ደኅንነት ጋር የተገናኙ ሥራዎችን የሚሠሩ የዘርፉ ባለሙያዎችም መጽሐፉን ቢያነቡት በእጅጉ ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡

መጽሐፉ እንግሊዝ ሀገር ለንደን በሚገኝ ዓለም አቀፍ አታሚ ድርጅት ደረጃውን ጠብቆ የታተመ ሲሆን አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ የሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መጽሐፉን ለማግኘት ለአታሚው ድርጅት ጥያቄ ማቅረባቸውን ዶ/ር አንቺት ጠቁመዋል፡፡ መጽሐፉን አሁን ኦን ላይን ገዝቶ መጠቀም የሚቻል መሆኑን የተናገሩት ጸሐፊው በቅርቡ በተለያዩ የመጽሐፍ መሸጫ መደብሮች ለሽያጭ ይቀርባልም ብለዋል፡፡

ዶ/ር አንቺት በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው ይህንን መጽሐፍ ለኅትመት እንዲያበቁ ለረዷቸው ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ ለቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር፣ ለኢንስቲትዩቱ ምርምርና ማኅበረሰብ አገ/ት ዳይሬክተርና ለሥራ ባልደረቦቻቸው ሁሉ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት