የሕግ ት/ቤት በሽግግር ፍትሕ አማራጮች ያለፉ ጉዳዮች መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ሕግ ተማሪዎች፣ መምህራንና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የተወጣጡ ግለሰቦች በተገኙበት ታኅሣሥ 12/2014 ዓ/ም ሴሚናር አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍና የሽግግር ፍትሕ ጉዳዮች መምህር ዶ/ር ማርሸት ታደሰ እንዳብራሩት የሽግግር ፍትሕ ያለፈውን በመነጋገር፣ እንደ ሀገር የተከሰቱ ጉዳዮችን በመቀበልና እውነቱን በማውጣት ወደ ፊት መሻገር ዋነኛው ዓላማው ነው፡፡ የሽግግር ፍትሕ ዋና ጽንሰ ሃሳብ ወደ ፊት ለማራመድ እንደ አንድ አማራጭ የሚያገለግል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ከተቋቋመ ጀምሮ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችና በሥራዎቹ ላይ የሕግ ክፍተቶች መኖር አለመኖራቸው፣ ኮሚሽኑ በተሻለ ሁኔታ እዲሠራ ማድረግ የሚጠበቅብን እገዛ፣ የሌሎች ሀገራት ልምድ እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ለመተግበር የዩኒቨርሲቲዎች ሚና በሴሚናሩ ገለጻ ከተደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የሕግ ት/ቤት መምህር አቶ ዳግም ወንድሙ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለፉ ክስተቶችን አስመልክቶ ሁለት ጽንፎችን የያዙ አካላት ያሉ ሲሆን አንደኛው ያለፈው ስህተት ተከድኖ ይብሰል (አይነካ) ሌላኛው ወገን ደግሞ እውነቱ ይውጣ የሚሉ ናቸው፡፡ የሽግግር ጊዜ ፍትሕን በመጠቀም እሳቤዎቹን ማስታረቅ እደሚቻል አቶ ዳግም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ይህን መሰል ውይይቶች ቢለመዱ በሀገር ደረጃ እየታቀደ ላለው ሀገራዊ መግባባት ጥሩ ግብዓት ይሆናል ብለዋል፡፡

በሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሃሳብ፣ በሽግግር ፍትሕ አማራጮች በኢትዮጵያ እና የመሳሰሉ ሃሳቦች ላይ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡