የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት በኮቪድ-19 ዙሪያ በተሠሩ 28 ምርምሮች ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ታኅሣሥ 22/2014 ዓ.ም ግምገማዊ ወርክሾፕ አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ቀውስን ያስከተለ መሆኑንና በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው ዩኒቨርሲቲውም በተለያዩ የመከላከልና የድጋፍ ሥራዎች የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ በወርክሾፑ በሽታውን ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ለመከላከል የሚረዱ ሃሳቦች የሚቀርቡ በመሆኑ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው እንደ ተቋም በተለይ የጤና ተቋማት የሕዝብን ሕይወት የሚታደግ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ ጥሪን ተቀብሎ መንግሥት በሽታውን ለመከላከል ያወጣቸው ስልቶችና የማኅበረሰቡ ግንዛቤ፣ የስርጭቱ ወቅታዊና ቀጣይ ሁኔታ እንዲሁም የመከላከያ መንገዶች ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ እስከ አሁንም 23 ምርምሮች የተጠናቀቁና 5ቱ በሂደት ላይ ያሉ ሲሆን ከ17 በላይ የሚሆኑ የምርምር ውጤቶች በሀገርና በዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ ለኅትመት በቅተዋል፡፡ ወርክሾፑ የምርምር ውጤቶችን ለማወቅና ቀምሮ ለሴክተሩ ግብዓት እንዲያገለግል ለማድረግ ብሎም ኮቪድ-19 ያልጠፋና ባህሪውን እየቀየረ የመጣ በመሆኑ በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ የሚመክር መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በበኩላቸው በኮቪድ-19 ወቅት ዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰቡን ሊረዱ የሚችሉ በምርምርና በቴክኖሎጂ ፈጠራ የተገኙ የእጅ መታጠቢያና ሳኒታይዘር ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ምርምሮችን ሲያካሂድ እንደመቆየቱ የግምገማ መድረኩ መዘጋጀቱ የምርምር ሥራዎቹ ያሉበትን ደረጃ ለመለየትና በባለድርሻ አካላት በማስገምገም ያላለቁት በምን ደረጃ ማለቅ እንዳለባቸው አቅጣጫ የምናስይዝበት ነው ብለዋል፡፡

የኬሚስትሪ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ከተማው ሳለልኝ በምርምራቸው ባህላዊ አረቄን በማጣራት ለሳኒታይዘር ትልቅ ግብዓት የሚሆነው ኢታኖል ደረጃ በማድረስ ሳኒታይዘር በማምረት ማሰራጨት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ በቀላሉ ገበያ ላይ የማይገኘውን ኢታኖል የሚመረትበትን ማሽን ሠርቶ በማሰራጨት መሳተፋቸውንና ይህም የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ መሰል የግምገማ መድረኮች መዘጋጀታቸው የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ የሚያግዙ፣ ድክመቶቻችንን የሚጠቁሙ፣ በሥራው ላይ የሚፈጠረውን ብዥታ የሚያጠሩና የሥራ መነቃቃትን የሚፈጥሩ ናቸውም ብለዋል፡፡

ሌላኛው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ አቶ አዲስ አክሊሉ ምርምሩን በጀመሩበት ወቅት ምንም ዓይነት ክትባት ባለመኖሩ በሽታ የመከላከል አቅምን ከማሳደግ አንፃር ኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ዕይታ በጥናታቸው መዳሰሳቸውን ገልጸዋል፡፡ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እቅስቃሴና ለሕፃናት የፀሐይ ብርሃን በሽታ የመከላከል አቅምን የሚጨምር በመሆኑ በዚያ ዙሪያ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ፣ አመለካከትና የትግበራ መጠን አጥንተዋል፡፡ በውጤቱም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ መሥራት እንደሚጠበቅብን ዐይተናል ብለዋል፡፡

ከቀረቡት ምርምሮች መካከል ‹‹knowledge, Attitude and Practice of the Community Towards Immune System Boosting Conditions to Fight Against COVID-19 in Gamo, Gofa and Konso Zones, Southern Ethiopia››፣ ‹‹Quality Improvement of Traditional Alcohol(Areke) With Re-Distillation Process to Produce Ethanol for Hand Rub Sanitizer Preparation to Avert Covid-19››፣ ‹‹Health Communication Strategies to Prevent the Expansion of Coronavirus Outbreak in Ethiopia at Local Government level Focusing on Some Selected Zones of SNNPR›› የሚሉት ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

በግምገማ መድረኩ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ ከጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች፣ ከአርባ ምንጭ ከተማና ከደራሼ ልዩ ወረዳ የመጡ የጤና መምሪያ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በመርሃ-ግብሩ ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት