የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በተለያዩ ወረዳዎች እየተሠሩ ያሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ሥራዎች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ታኅሣሥ 25/2014 ዓ/ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ እየተሠሩ ያሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ሥራዎች፣ ያሉባቸው ችግሮችና የ2014 ዓ/ም የችግኝ ስርጭት ዕቅድ በውይይቱ ተነስተዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት በማኅበረሰብ አገልግሎት ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ችግሮችን ለመፍታት ለአንድ ዓላማ በጋራ ከሚቆሙ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለው ግንኙነት የአየር ንብረት ቀውስ፣ የብዝሃ ሕይወት መመናመንና የአካባቢ ብክለት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ መፍትሔ ለማፈላለግ በአካባቢና ተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ሁላችንም በጋራ ተቀናጅተን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ረ/ፕ ይበልጣል ይሁኔ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል የአካባቢና ደን ጥበቃ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ከ8 በላይ ወረዳዎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት መግባባትን ለመፍጠር የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ውይይቱ እስከ አሁን የተሠሩ ሥራዎችን ለሚመለከተው አካል ለማሳወቅ፣ የባለድርሻ አካላትን ሚና ለይቶ ለመስጠትና የተሻለና የዘመነ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የውይይት መድረኩ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚረዳ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በአረንጓዴ ልማት በሚያከናውናቸው ሥራዎች እንደ ባለድርሻ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት