የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ለተማሪዎች አደረጃጀት፣ ለክበባት አስተባባሪዎችና ለሴት ተማሪዎች መኝታ አስተባባሪዎች ታኅሣሥ 23/2014 ዓ/ም የካምፓስ ሕይወት አማካሪነት/ Campus Life Mentorship/ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዳይሬክቶሬቱ ባለሙያ ወ/ሮ አበበች አዳነ እንደገለጹት ሥልጠናው በዋናነት የማማከር አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሲሆን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ፣ እርስ በእርስ እንዲተጋገዙ፣ ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ እንዲመካከሩና ጤናን ከሚጎዱ ሱሶች ራሳቸውን ጠብቀው ጤናማ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ወ/ሮ አበበች ስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደትና ሰላማዊ የትምህርት ተቋም እንዲኖር ተማሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውና ለራሳቸውና ለሀገራቸው የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከሥልጠናው በኋላ የአማካሪ ባህርያትን በመላበስ ለአዳዲስ ተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ማዘጋጀትና በተደጋጋሚ ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ማፈላለግ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሀገሪቱ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ በርካታ ተማሪዎች ወላጆቻቸውን አጥተው ከመማር ማስተማር፣ ከጤና፣ ከሥነ-ልቦናና ከማኅበራዊ ጉዳዮች አንፃር ችግሮች የደረሱባቸው በመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ በጋራ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት