በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር መለሰ መንገሻ ‹‹EASY WAYS TO READ IN ENGLISH›› በሚል ርዕስ ከKG - 4ኛ ያለውን የክፍል ደረጃ መሠረት አድርጎ የተዘጋጀው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፍኖተ ንባብ አጋዥ መጽሐፍ ታኅሣሥ 26/2014 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ተመርቋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ መጽሐፉ የንባብ ችግርን በምርምር ለይቶ ከመሠረቱ ለመፍታት ጥረት የተደረገበትና መሰል ምላሾችን የያዘ በመሆኑ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ይሰጣል ብለዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማሳካት ከታች ጀምሮ ሊሠራ ይገባል ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ የቀረበው መጽሐፍም ለዚህ ግብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገግልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲነቱ የኅትመት ሥራዎችን በዕቅድ ይዞ የሚሠራ በመሆኑ ሁላችንም የትምህርት ጥራት ችግርን በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርምሮችን በማካሄድ መሰል ሥራዎችን ልንሠራና የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናበረክት ይገባል ብለዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር መለሰ መንገሻ በመምህርነት ቆይታቸው በርካታ የንባብ ክሂል ክፍተቶችን በማስተዋላቸው ችግሩን ለመለየት የተለያዩ የተግባር ትምህርቶችን በመስጠት ጥናት ማካሄዳቸው መጽሐፉን ለማዘጋጀት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡ ከጥናቱ ያገኙትን ውጤት መሠረት በማድረግ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ንባብ ክሂል መማሪያና ማስተማሪያ የሚሆን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፍኖተ ንባብ መጽሐፍ ማዘጋጀታቸውን ዶ/ር መለሰ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መለሰ የትምህርት ጥራትን እስከ መጨረሻው ለማስጠበቅ መሠረት በሆነው ታችኛው ክፍል ላይ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም የተሻለ ዕውቀት ያለውን መምህር መመደብና የተሻሉ የመማሪያ መጻሕፍትን በማዘጋጀት በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል፡፡

የመጽሐፉ ገምጋሚና አርታኢ የሆኑት የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ተስፋዬ ዓለሙ እንደገለጹት መጽሐፉ ምርምርን መሠረት ያደረገ፣ ከችግር ተነስቶ መፍትሔ የሚፈልግና በተግባር ተመዝኖ በቀጥታ ለውጥ ማምጣቱ የታየ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ መጽሐፉ ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፊደላትንና ድምጾችን ገጣጥመው ቃላትን ሲጠሩ ለሚፈጥሩት ስህተት መፍትሔ የሚሰጥ፣ ከሽፋን ገጹ ጀምሮ ዓይንን ሳቢና ማራኪ፣ ቃላት ከስዕሎች ጋር እንዲናበቡ ተደርገው የቀረቡበት እንዲሁም ተማሪዎች የንባብ ክሂላቸውን በቀላሉ በመለማመድ እንዲያዳብሩ የሚረዳቸው ሆኖ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ መሰል ሥራዎች በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡ ጥያቄ የለውም ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ ሥራው ብዙ ልፋትና የገንዘብ ወጪ እንዲሁም ትዕግሥትን እና ፈቃደኝነትን የሚጠይቅ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህር አቶ ፍስሃ በቀለ በዕለት ከዕለት ተሞክሮዎች የዳበረ፣ የላቀ ውጤት ያስገኘ፣ በቀላል አቀራረብ የተከሸነና ለዕይታ ማራኪ የሆነ መጽሐፍ ለማስመረቅ በመብቃታቸው ለአዘጋጁ የተሰማቸውን

ደስታ ገልጸዋል፡፡ አቶ ፍስሃ የሀገራችን ሕፃናት ቢያንስ 4ኛ ክፍል ሲደርሱ በአፍ መፍቻም ሆነ በ2ኛና በውጪ ቋንቋዎች አቀላጥፈው እንዲያነቡ ለማስቻል በእጅጉ የሚረዳ በመሆኑ ማኅበረሰቡ መጽሐፉን በመጠቀም የትሩፋቱ ተቋዳሽ እንዲሆን የማንቃት፣ የማሳወቅና የመደገፍ ሥራ በማከናወን ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡

ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ችግሩን ከመሠረቱ ለመቅረፍ ከአጸደ ሕፃናት ጀምሮ የሚያስተምሩ መምህራን የተሻለ ዕውቀት ያላቸው ሊሆኑና ወላጆችም የታችኛው ክፍል መሠረት መሆኑን አውቀው ልጆቻቸውን ማስጠናትና መሠረት ማስያዝ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ችግሩ በዘላቂ ሁኔታ የሚፈታበት ፕሮጀክት ቢቀረጽና ቢሠራ የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣም ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት