በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ከግንባታ ዘርፍ ጋር የተያያዘ ትምህርት ለሚሰጡ መምህራን፣ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችና በዘርፉ እየሠሩ ላሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤትና የዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች ‹‹Effective Project Planning and Monitoring›› በሚል ርዕስ ከታኅሣሥ 25-26/2014 ዓ.ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በእንግሊዝ ሀገር የ‹‹McGEE›› ካምፓኒ የፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትና በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ በተላለፈው ሀገራዊ ጥሪ መሠረት ወደ ሀገር ቤት የመጡት አቶ ለም በሪሁን በዩኒቨርሲቲው አልሙናይ ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ ጋባዥነት ሥልጠናውን እንዲሰጡ መመቻቸቱ ተገልጿል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በግንባታው ዘርፍ አዳዲስ ክሂሎቶችን በመቅሰም እንደ ሀገር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና ክፍተቶችን ለመሙላት ሥልጠናው ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በግንባታ ሥራዎች ላይ የሚታዩ የሥራ መጓተት ክፍተቶችን ለመሙላትና ሥራዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመሥራት ያግዛልም ብለዋል፡፡

አሠልጣኝ ለም በሪሁን በበኩላቸው አብዛኛው ፕሮጀክቶች በተወሰነላቸው የጊዜ ገደብና በጀት ለማጠናቀቅ ፈተናዎች እንደሚያጋጥማቸው ጠቅሰው አንድን ፕሮጀክት በታለመበት መንገድ ለማከናወን ውጤታማ የሚያደርጉ ቴክኒኮችን መለየትና መጠቀም በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ያደጉ ሀገራት እንደ ዋነኛ ጉዳይ የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ፕሮጀክቶችን መጀመር፣ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር፣ የአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ የአየር ሁኔታና ሌሎችም ምክንያቶች የግንባታ ሥራዎች እንዲስተጓጎሉ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ የተናገሩት አሠልጣኙ መሰል ችግሮችን ለማስወገድ የተሻሉ የሚባሉ ዘዴዎችን ካገኙት ልምድ በመነሳት በሥልጠናው ለማሳየት መሞከራቸውን ገልጸዋል፡፡

ቀልጣፋና በአግባቡ ተግባር ላይ መዋል የሚችል ዕቅድ ማዘጋጀት፣ የግንባታ ንድፍ አመራር፣ ፕሮጀክቶችን በማያደናቅፍ መልኩ ችግሮችን መቆጣጠር፣ ተወዳዳሪና የተሻሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዝግጅት እንዲሁም ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው አስቀድሞ የታሰቡ ግምቶች ከግንዛቤ ሳይገቡ ሥራዎችን ማካሄድ የሚያመጣው ተጽዕኖና መስተጓጎልን መቆጣጠር በሥልጠናው ከተቃኙ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የሲቪል ምኅንድስና እና የአርክቴክቸርና ከተማ ፕላን ፋከልቲዎች መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ በቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሥር ያሉ የግንባታ ዘርፍ ባለሙያዎች እና ከአርባ ምንጭ ከተማ የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በሥልጠናው ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት