አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት፣ ሶፍትዌር፣ የዌብ ጂ.አይ.ኤስ (GIS)ና የጂኦዳታቤዝ አስተዳደር መተግበሪያዎች አቅራቢ ድርጅት ከሆነው ‹‹Environmental Systems Research Institute (ESRI)›› ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ለመማር ማስተማር፣ ለምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ፈጠራና አስተዳደራዊ ሥራዎች የሚውል ‹‹ArcGIS›› ሶፍትዌርን ለ3 ዓመታት በነፃ የመጠቀም ፈቃድ አግኝቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በሶፍትዌሩ አጠቃቀምና በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅና ት/ቤት ዲኖች እንዲሁም የት/ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት ጥር 5/2014 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደገለጹት ኮሌጁ በጂ.አይ.ኤስና ሪሞት ሴንሲንግ ዘርፎች የምርምርና የሥልጠና ማዕከል ለመሆን እየሠራ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተደረገ የትብብር ስምምነት መሠረት ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩቶች ጋር በትብብር እየሠራ ነው፡፡ ከ‹‹ESRI›› ጋር በጋራ መሥራት በመጀመራችን ከተቋሙ ያገኘነው ነፃ የሶፍትዌር መተግበሪያዎች ለዩኒቨርሲቲያችን መምህራንና ተማሪዎች የሚያስገኘው ፋይዳ ጉልህ በመሆኑ የተገኘውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ከድርጅቱ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና የመግባባቢያ ስምምነት እንዲፈራረሙ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ዕድሉን እንዲያገኝ ላስቻሉት ለመ/ር ደንበል ቦንታም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል የጂ.አይ.ኤስና ሪሞት ሴንሲንግ መምህር አቶ ደንበል ቦንታ ‹‹ESRI›› በአሜሪካ ሀገር የሚገኝ ዓለም አቀፍ የጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት፣ ሶፍትዌር፣ የዌብ ጂ.አይ.ኤስና የጂኦ ዳታቤዝ አስተዳደር መተግበሪያዎች አቅራቢ ድርጅት መሆኑን ተናግረው ከተቋሙ ጋር ግንኙነት በማድረጋችን እንዲሁም ዘርፉን ለማሳደግ እንደ ዩኒቨርሲቲ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በማስገንዘባችን ተቋሙ ሶፍትዌሩን በነፃ እንድንጠቀም ፈቃድ ሊሰጠን ችሏል ብለዋል፡፡ ‹‹ArcGIS›› ሶፍትዌር በሥሩ በርካታ መተግበሪያዎችን በመያዝ የስፓሻል ዳታ ትንተናዎችን፣ የመስክ ላይ ሥራዎችን፣ ካርታዎችን ለመፍጠር፣ ለመጠቀምና ለማጋራት፣ ለኢሜጅሪና ሪሞት ሴንሲንግ ሥራዎችን ለማከናወን፣ መረጃዎችን ወደ 3D ለመቀየር እንዲሁም ለመረጃ መሰብሰብና ለማስተዳደር እንደሚያግዝ አቶ ደንበል ተናግረዋል፡፡ በተለይ ለምርምር ሥራዎች ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብና ለመተንተን ሲባል ከዚህ ቀደም የሚጠፋውን ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ከማስቀረቱም ባሻገር ትክክለኛና ተአማኒ መረጃ አሰባሰብና የትንተና ሂደት እንዲኖር ያደርጋልም ብለዋል፡፡

የተገኘው ነፃ ፈቃድ ለዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች ትልቅ ዕድል ነው ያሉት መምህሩ ይህም ክራክ የተደረጉ ሕጋዊ ያልሆኑ ሶፍትዌሮችን ከመጠቀም ተቋሙንና መምህራኑን የሚያላቅቅ ሲሆን ፈቃድ ያላቸውን መተግበሪያዎች በመጠቀም የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ እንደ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ የሚታተሙ የምርምር ሥራዎችን ቁጥር ይጨምራል ብለዋል፡፡ ተቋሙ ለዩኒቨርሲቲው ለ3 ዓመታት የሚቆይ ከ15 ሚሊየን በላይ ክሬዲቶች ያሉት ፈቃድ የሰጠ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም የተሰጠው ፈቃድ ዘላቂ እንዲሆን አጠቃቀማችን ወሳኝ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አካውንት በመክፈት ሶፍትዌሩን በአግባቡ መጠቀም አለበት ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ከድርጅቱ የተገኘው ነፃ ሶፍትዌር እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠትና ጥራት ያላቸው የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ብሎም አስተዳደራዊ ሥራዎችን ዲጂታላይዝ ከማድረግ አኳያ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች ሶፍትዌሩን መጠቀም እንዲችሉ ሥራዎች ታቅደው በስፋት ሊሠሩ እንደሚገባና ሥራውን የሚያስተባብር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በማቋቋም ለዘርፉ ዕድገት እንደሚሠራም ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ሶፍትዌሩ በዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች በሚገኙ የኮምፕውተር ማዕከላት የተጫነ በመሆኑ ሶፍትዌሩን መጠቀም የሚፈልጉ የዩኒቨርሲቲው አባላት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ላይ የዩኒቨርሲቲ መታወቂያቸውን ስካን አድርገው ኢ-ሜይል በማድረግ አካውንት መክፈት እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ በሚቋቋም ጊዜ ሥልጠናዎች በስፋት የሚሰጡ መሆኑም በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት