የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በኃላፊነት ላይ ላሉ ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የአመራርና የአስተዳደር ክሂሎት እንዲሁም ለጸሐፊዎችና የቢሮ ረዳቶች በሥርዓተ ጾታ፣ ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃትን በመከላከል ላይ ከጥር 04 - 06/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ሥልጠናው እርስ በእርስ መማማሪያ፣ ወደ አመራር ያልመጡ ሴት መምህራንና ሠራተኞች ለመምጣት እንዲነሳሱና አመራር ላይ ያሉትም አቅም በማጎልበት በተሻለ ደረጃ እንዲተጉ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ በጾታና በሥርዓተ-ጾታ መካከል ያለውን ልዩነት ተረድቶ በተዛባ የሥርዓተ-ጾታ አሰላለፍ የተነሳ በሚከሰተው ጾታዊ ጥቃት የማይሳተፍ፣ የማይተባበርና ሲከሰትም በዝምታ የማያልፍ ማኅበረሰብ እንዲኖር ማስቻል ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሠልጣኞችም ሁሉ አቀፍ የሆነ የአመለካከትና የክሂሎት ለውጥ በማምጣት ከግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ተሞክሮ ወደ ተግባር መቀየር ይገባል ብለዋል፡፡

አሠልጣኞች ገሊላ ቢረሳውና አስቴር ሰይፉ ሴቶች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ ያህሉን ቢይዙም በኃላፊነት ቦታዎች ላይ በእኩል ደረጃ ተወካይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ሴቶች የመሪነት ምንነትን ዐውቀው በድፍረት፣ በራስ በመተማመንና እችላለሁ በሚል ስሜት ወደ ኃላፊነት ለመምጣት መነቃቃት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ ሴቶችን ወደ አመራር ማምጣት ብቻ ሳይሆን ወደ ከፍተኛ አመራር ደረጃ እንዲመጡና ራሳቸውን በተመለከቱ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ማነሳሳትና ማብቃት የሥልጠናው ዓላማ መሆኑን አሠልጣኞቹ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሴቶች ወደ አመራር እንዳይመጡ የሚያደርጉ መሰናክሎችን የሚያልፉበት ዘዴዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የጾታና የሥርዓተ-ጾታ ምንነት፣ በጾታና በሥርዓተ-ጾታ መካከል ያሉ ሳይንሳዊ ልዩነቶች፣ በሀገራችን በሁለቱም ጾታዎች መካከል የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች፣ መሠረታዊ የሥርዓተ-ጾታ የግንዛቤና የአመለካከት ለውጥ መፍጠሪያዎች እንዲሁም የአመራርና የአስተዳደር ክሂሎት በሥልጠናው የተካተቱ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኙ የሥራ ክፍሎች የሁለቱንም ጾታዎች እኩል ተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲያዳብሩ ለማድረግና ሴቶች በሴትነታቸው ምክንያት የሚመጡ የአመለካከት ዝንፈቶችን በመቀየር ሠርተው በሚያስመዘግቡት ውጤት ከወንድ አቻቸው ጋር እኩል ተሳታፊነታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው በሥልጠናው ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት