በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ላላፉት 5 ዓመታት የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት እጩ ዶ/ር እንደልቡ ጎኣ የምርምር ሥራቸውን ጥር 14/2014 ዓ/ም የውጪና የውስጥ ገምጋሚዎች በተገኙበት አቅርበው ተገምግሟል፡፡የመመረቂያ ጽሑፉም አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡   

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማግኘት በተለያዩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በ2009 ዓ/ም አጋማሽ ላይ የጀመሩት እጩ ዶ/ር እንደልቡ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ‹‹The Effect of Bottom-up Continuous Professional Development (CPD) Approach on English Language Teachers Perception, Self-Efficacy, Beliefs and Pedagogic Effectiveness›› በሚል ርዕስ ላይ አከናውነዋል፡፡  

እጩ ዶ/ር እንደልቡ ጎኣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ 7ኛው እንዲሁም በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያው የ3ኛ ዲግሪ ምሩቅ መሆናቸውን የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ዩኒቨርሲቲው ከአካዳሚክ ዩኒቨርሲቲነት ወደ ምርምር ዩኒቨርሲቲነት እንደ መሸጋገሩ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በማስፋፋት ላይ እንዲሁም የመማር ማስተማሩን ሂደት ምርምር ተኮር በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡    ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የድኅረ-ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት ማስመረቅ መጀመሩን አስታውሰው ይህም እንደ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው ለድኅረ-ምረቃ ትምህርት መስክ ዕድገት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን በተለይም የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በወቅቱ የመመረቅ ምጣኔን ለማሳደግ የሚያስችል መመሪያ አጽድቆ በቅርቡ ወደ ሥራ አስገብቷልም ብለዋል፡፡ ፕሮግራሞችን ከማስፋፋት አንፃርም በዚህ ዓመት 13 የ2ኛና 1 የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች የተከፈቱ ሲሆን በተጨማሪም በዚሁ ዓመት 6 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመክፈት እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር አበራ ጠቁመዋል፡፡

እጩ ዶ/ር እንደልቡ የዶክትሬት ዲግሪያቸው በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ከጸደቀ በኋላ የሚያገኙ ሲሆን በዛሬው መርሃ-ግብር ላይ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትን ጨምሮ፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የዘርፉ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት