የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አውስትራሊያ ሀገር ከሚገኘው ‹‹Menzies School of Health Research›› ከተሰኘ የጤና ምርምር ት/ቤት ጋር ‹‹Effectiveness of Novel Approaches to Radical Cure of Vivax Malaria with Tafenoquine and Primaquine›› በሚል ርዕስ የሚያከናውኑትን ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት መጀመር የሚያስችል በ‹‹Clinical Trial›› የምርምር ሥነ-ምግባርና ፕሮቶኮሎች ዙሪያ በምርምሩ ለሚሳተፉ ስፔሻሊስት ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች ከት/ቤቱ በመጡ ባለሙያ ከጥር 13/2014 ዓ/ም ጀምሮ ለ5 ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የምርምር ፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለጹት የምርምር ፕሮጀክቱ በዋናነት ቫይቫክስ ተብሎ ለሚጠራው የወባ በሽታ ዓይነት የሚሰጡ ‹‹Tafenoquine›› እና ‹‹Primaquine›› የተሰኙ መድኃኒቶችን ውጤታማነት፣ ፈዋሽነትና የጎንዮሽ ጉዳቶችን መፈተሽን ዓላማ በማድረግ በሦስት ቡድን በተከፈሉ 350 ሰዎች ላይ ለ6 ወራት ሙከራና ክትትል በማድረግ የሚከናወን ነው ብለዋል፡፡ የምርምር ሥራውን ለመጀመር የሚያስችሉ ግብአቶችን አሟልተናል ያሉት ዶ/ር ታምሩ በምርምሩ ለሚሳተፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የተሰጠው ሥልጠናም የምርምር ሥራው ውጤታማና የታለመለትን ግብ እንዲመታ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምርምሩ ሲሠራ ለታማሚዎች መደረግ ያለበት አቀባበልና መስተግንዶ፣ ክትትል፣ የመድኃኒት አሰጣጥ፣ ታማሚዎችን የመለያ ዘዴዎች፣ የመረጃ አያያዝ፣ የላቦራቶሪ ምርምራ ዓይነቶች ወዘተ የሥልጠናው ትኩረቶች መሆናቸውን ዶ/ር ታምሩ ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት ወ/ሪት ሔለን ሜሲ ምንጃላ (Ms Hellen Mesi Mnjala) እንደገለጹት መሰል የምርምር ሥራዎች በሚከናወኑ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት የሚፈልጉ በመሆናቸው በምርምር ሥራው ላይ የሚሳተፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑ ጊዜ ሊከተሏቸው በሚገቡ የምርምር ሥነ-ምግባርና ፕሮቶኮሎች ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበት ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ ተቋማቸው መሰል የምርምር ሥራ በካምቦዲያና ኢንዶኔዥያ የሚያካሂድ መሆኑን የጠቆሙት አሠልጣኟ ከሥልጠናው የሚገኘው ግንዛቤ ለምርምር ሥራው ውጤታማነትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምርምር ውጤት ለማግኘት ያለው ፋይዳም ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጥናቱ የሚሳተፉ ተመራማሪዎችም ሆነ ባለሙያዎች የተቀመጡ የምርምር ሥነ-ምግባር መርሆዎችንና ፕሮቶኮሎችን በመከተል የምርምር ሥራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ቫይቫክስ የተሰኘው የወባ በሽታ ዓይነት በጉበት ውስጥ ተደብቆ በመቆየት ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ በተደጋጋሚ የመከሰት ባህሪ ያለው ሲሆን የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረትም ለበሽታው በሦስት ዓይነት መንገድ የሚሰጡትን ሁለቱን መድኃኒቶች ለታማሚዎች በመስጠትና ለ6 ወራት ክትትል በማድረግ የትኛው መድኃኒትና ዘዴ ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነና ዳግም በሽታው በጉበት ውስጥ ተደብቆ እንዳይነሳ የማድረግ አቅም እንዳለው መለየት ነው፡፡ አነስተኛ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትለውን የመድኃኒት ዓይነትና ዘዴ መለየት ሌላኛው የምርምር ሥራው ትኩረት ሲሆን ጥናቱም ከአርባ ምንጭ

ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በተወጣጡ 3 ስፔሻሊስት ዶክተሮች፣ 5 የላቦራቶሪ ባለሙያዎች፣ 3 ነርሶችና 2 የፋርማሲ ባለሙያዎች ይከናወናል፡፡

የምርምር ፕሮጀክት ሥራው ሦስቱ ተቋማት በጋራ ለመሥራት ጥቅምት 5/2014 ዓ/ም በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት የሚፈጸም ሲሆን ‹‹Menzies School of Health Research›› ለፕሮጀክቱ የሚሆን 210 ሺህ ዶላር መድቧል፡፡ የምርምር ሥራው ከጥር 24/2014 ዓ/ም ጀምሮ በይፋ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት