አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕወሓት ወራሪ ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ላጋጠመው ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ማስተማር ሥራ የሚውሉ ላፕቶፖች፣ ወረቀቶች፣ ካኪ ፖስታዎች፣ እስክሪብቶዎች፣ ቾክ፣ የቢሮና የተማሪ ወንበሮች፣ የማስተማሪያ ጠረጴዛዎች፣ ለተማሪ የምግብ አገልግሎት የሚውሉ የካፍቴሪያ ዕቃዎች፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ፕላስቲክ ጋኖች፣ የእንጀራ ምጣዶች፣ የፍራሽ፣ የዕቃ ማመላለሻ ጋሪዎችና የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ጥር 21 እና 22/2014 ዓ.ም በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ድጋፍ አድርጓል፡፡ የቁሳቁስ ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን 2.5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡

    ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና ድጋፉን ያስረከበው ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ካጋጠማቸውና ትምህርት መስጠት ያቋረጡ የትምህርት ተቋማት መካከል ወልድያ ዩኒቨርሲቲ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የውስጥ አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በመውደሙና አሁን ባለው ቁመና ለመማር ማስተማር ሂደት ብቁ ባለመሆኑ እንደ ሀገር ዩኒቨርሲቲውን ለመደገፍ ከተለዩ 9 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አንዱ በመሆኑ ድጋፉ መደረጉን ዶ/ር ተክሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተክሉ ገለጻ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ልዑካን ቡድን የወልድያ ዩኒቨርሲቲን አሁናዊ ሁኔታ ምልከታ ያደረገ ሲሆን ቤተ-ሙከራዎች፣ ወርክሾፖችና የኤሌክትሪክ መስመሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ተመልክቷል፡፡ ዶ/ር ተክሉ በተለይ የሕንፃው ውስጣዊ አደረጃጀት እንደ አዲስ መሠራትና ጥገና የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲጀምር ዩኒቨርሲቲዎች የጀመሩትን ድጋፍ ማስቀጠል እንደሚገባቸውና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ያጋጠማቸውን የትምህርት ተቋማት ለመደገፍ በክላስተር ደረጃ ከተዋቀሩ 9 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሐሮማያና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት