በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ት/ክፍል የ2ኛ ዓመት ተማሪ የነበረችው ጽጌረዳ ግርማይ በቅርብ ጓደኛዋ ተማሪ በደረሰባት የስለት ጥቃት ጥር 23/2014 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን አስመልክቶ በኮሌጁ አስተባባሪነት የካቲት 01/2014 ዓ/ም የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ በፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት የሐዘን መልዕክት በተማሪ ጽጌረዳ ላይ የደረሰው ጥቃት ልብ የሚሰብርና አሳዛኝ ክስተት መሆኑን ገልጸው በተማሪዋ ኅልፈት ምክንያት በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ተጠርጣሪ የሕግ ሂደቱ ተፋጥኖ ውሳኔ ተሰጥቶት ሁላችንም ፍትሕን በአደባባይ ማየት እንሻለን ብለዋል፡፡ የካምፓሱ ተማሪዎች እንዲረጋጉና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የተማሪዋ ድንገተኛ ኅልፈት እጅግ በጣም አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የሰው ልጅ እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረው ትልቅ ፍጡር በመሆኑ ክብር ልንሰጠው እንዲሁም እንኳን በጭካኔ ልንጎዳ እንዳናስቀይም መጠንቀቅ የሚገባ ነው እንጂ ሕይወቱን በዚህ ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ በማጥፋት በሰማይም ሆነ በምድር የሚያስጠይቅ ሥራ ልንሠራ አይገባም ብለዋል፡፡

ዶ/ር ዳምጠው ከሕግ ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ በሚመለከተው ክፍል በትኩረት ክትትል እንደሚደረግበት ጠቁመው ለቤተሰቦቿ፣ ለወዳጅ ዘመዶቿ፣ ለጓደኞቿ እንዲሁም በኅልፈተ ሕይወቷ በእጅጉ ላዘነው ለዩኒቨርሲቲውና ለውጪው ማኅበረሰብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው ክስተቱ ሴት በመሆን ብቻ የሚመጣ አይደለምና ሁሉም ለወላጆቻቸው ውድና አስፈላጊ እንደመሆናቸው መጠን ራሳቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡ አክለውም የልጃችንን ነፍስ ይማርልን፤ ለቤተሰቦቿና ለጓደኞቿ እንዲሁም ላዘነው ሁሉ ሰማያዊ የሆነ መጽናናትን ይስጥልን ብለዋል፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደ ሴትም እንደ ሰውም በተማሪ ጽጌረዳ ላይ የደረሰው ግድያ ልባቸውን የሰበረው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ሥራ ክፍል ከተቋሙ የሕግ አገልግሎት ጋር በመሆን ክትትል የሚያደርጉና ፍትሐዊና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ የሚሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሯ አክለውም በተለይ ሴቶች ማንኛውም የሚያሰጋችሁ ሁኔታ ሲገጥማችሁ አስቀድማችሁ ለት/ክፍል ኃላፊዎች፣ ለፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም ለሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች የሥራ ክፍሎች ጥቆማ ብታደርጉ መሰል አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ለመከላከልና የሰውን ሕይወት ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳል ብለዋል፡፡

‹‹ለቁም ነገር ስትጠበቅ ወጥታ መቅረቷ ያሳዝናል›› ያሉት የጫሞ ካምፓስ የሴት መምህራን ተወካይና የሆቴልና ቱሪዝም ት/ክፍል መምህርት አዜብ ታምራት ሁሉም ተማሪዎች ዙሪያቸውን ሊያዩ እንደሚገባና ከክፉ ነገር ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የሰዎችን ጥቃት ለማስቀረት ሁሉም በጋራ እንዲቆም፣ ሴት ልጅ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ሲደርስባት እያየ አልፎ የሚሄድ ወንድ እንዳይኖርና ሁሉም ይመለከተኛል ብሎ ችግሩን እንዲፈታ አልያም ጥቃቱን እንዲከላከል ጠይቀዋል፡፡ በተማሪ ጽጌረዳ ኅልፈት ላዘኑ ሁሉ በትምህርት ክፍላቸው ስም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት የጫሞ ካምፓስ ተወካይ ተማሪ ማኅሌት ሰሎሞን እህታችንን ያጣንበት መንገድ አሳዛኝና ተገቢ ያልሆነ ነው ብላለች፡፡ ተማሪዎች ራሳቸውን እየጠበቁ በመረጋጋት ትምህርታቸውን መቀጠል እንዳለባቸውም ተናግራለች፡፡

የተማሪ ጽጌረዳ ጓደኞች የሚወዷት እህታቸውንና ጓደኛቸውን ባላሰቡትና ባልጠበቁት መንገድ ከአጠገባቸው ስላጧት ሐዘናቸው መሪርና የማይረሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሁላችንም ተማሪዎች የመጣነው አንድ ዓይነት ዓላማ ሰንቀን እንደመሆኑ እርስ በእርሳችን ሌላ ወገን ጥቃት እንዳያደርስብን ልንጠብቅ እንጂ አንዳችን በሌላችን ላይ ጥቃት ልናደርስ ባልተገባ ነበር ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እስከ መጨረሻው ከሕግ አካላት ጎን በመሆን ይህንን አሰቃቂ ወንጀል የፈጸመው ተማሪ ለሌላውም አስተማሪ የሆነ ተገቢ ቅጣት እንዲያገኝ እንዲያደርግና ውጤቱንም እንዲያሳውቅም ጠይቀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና ም/ፕሬዝደንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳር ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን የሕሊና ጸሎት፣ የተለያዩ የሐዘን መግለጫዎችና ግጥሞች ቀርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት