የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ከ6ቱ ካምፓሶች የተለያዩ ሥራ ክፍሎች ለተወጣጡ አስተባባሪዎች፣ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ከየካቲት 01-02/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በሥልጠናው የአእምሮ ዕውቀት፣ የስሜት ልህቀት፣ ስብእናና ተፈጥሯዊ ባህሪያት በስፋት ተዳሰዋል፡፡ 

 

የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንትና የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደተናገሩት ተቋም የሚገነባው በበቃ የሰው ኃይል አደራጀጀትና በግዑዙ መሠረተ ልማት ሲሆን የሰውን ልጅ ክሂሎት ለመለወጥ ሥልጠና መውሰድ፣ ማንበብ፣ መማርና ልምምድ ማድረግ ትልቅ ሚና አለው፡፡ ሁሉም ሠራተኛ ባለበት የሥራ ክፍል በኃላፊነት ሥራውን መወጣት፣ ያገኘውን ዕውቀት ለሌሎች ማስተላለፍ፣ ለሥራው ታማኝና የሥራ ሰዓት አክባሪ በመሆን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት ም/ፕሬዝደንቷ ገልጸዋል፡፡ የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ሠራተኛውን የማብቃት ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ከአዳዲስ ሃሳቦችና ግንዛቤዎች ጋር በማስተዋወቅ ሠራተኛው ንቁ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ወ/ሮ ታሪኳ አሳስበዋል፡፡   ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ የሰው ኃይሉ ዋና ፈፃሚ እንደ መሆኑ ተቋሙን ውጤታማ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የሰው ሀብትን በምንፈልገው ደረጃ ካልገነባነው የምንፈልገውን ውጤት ማምጣት ስለማይቻል መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ በበኩላቸው ሥልጠናው አዳዲስ ሃሳቦችን በማስተዋወቅና የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር ውጤት የሚያመጣ ንቁ ሠራተኛን ለማፍራት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው የአመራሩን አመለካከትና አስተሳሰብ በመቀየር ከታች ላሉት አካላት የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሳለጥ ባሻገር አገልጋዩ ራስ ወዳድ፣ አገር ወዳድ፣ ቅንና ታማኝ ስብዕና ያለው ዜጋ እንዲሆን እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በግል ራሳችንን እንድናይና ክፍተቶቻችንን እንድንረዳ ዕድል የፈጠረልን ሲሆን ደንበኞቻችንን እንዴት ማስተናገድ እንዳለብንና ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ የሚረዳ ግንዛቤ ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት