በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በሂሳብ ት/ክፍል ላለፉት 5 ዓመታት የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት እጩ ዶ/ር መኮንን ሬዲ የካቲት 11/2014 ዓ/ም የውስጥና የውጪ ገምጋሚዎች በተገኙበት የምርምር ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የመመረቂያ ጽሑፋቸው ‹‹Water Allocation Optimization Under Conflicting Demand & Supply at Watershed Scale፡ The Case in Gidabo Dam and Gidabo Watershed, Ethiopia›› በሚል ርዕስ የተከናወነ ሲሆን አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ በመገኘቱ በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

እጩ ዶ/ር መኮንን ሬዲ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ 5ኛ እንዲሁም በት/ክፍሉ 2ኛው የ3ኛ ዲግሪ ምሩቅ መሆናቸውን የገለጹት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች የበለጠ ምቾት እንዲሰማቸውና በአካዳሚክና ምርምር ሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ዘመኑ የፉክክር ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዓለማየሁ ለተማሪዎቻችን የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች በማሟላት ራሳችንን መለወጥ፣ በጥናት ተኮር የመማር ማስተማር ሂደት ላይ በማተኮር መሥራትና በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ብቁ የሆኑ ምሩቃንን ማፍራት ይኖርብናልም ብለዋል፡፡
የሒሳብ ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ስምዖን ደርኬ በግምገማው ላይ ከፈታኞች ከተነሱት ጥያቆዎችና አስተያየቶች በቅርቡ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን ጨርሰው ያስገቡና ሊጨርሱ የተቃረቡ ተማሪዎች ተገቢውን ትምህርትና ልምድ የሚወስዱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እጩ ዶ/ር መኮንን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ ጥናታቸው ለእርሻ፣ ለቤት አገልግሎት፣ ለኢንደስትሪና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚውል ውሃ ፍላጎትና አቅርቦት መጠን አለመጣጣምንና ግጭቶችን ለመቅረፍ ዘልማዳዊ አሠራሮችን ማስቀረት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡