የስብእና ግንባታ አነቃቂና የቢዝነስ ሥራዎች አማካሪ ወጣት ማንያዘዋል እሸቱ ‹‹ራስን ማወቅ፤ ለዓላማ መኖር›› በሚል መሪ ቃል ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዋናው ግቢና በጫሞ ካምፓስ በስብዕና ግንባታ ዙሪያ የካቲት 10/2014 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ከተማ ተወልዶ ያደገው ወጣት ማንያዘዋል እሸቱ በዋናነት ለወጣቶች አነቃቂና አስተማሪ የሕይወት ክሂሎት መረጃዎችና መሠረታዊ የአስተሳሰብና የስብእና ግንባታ ጉዳዮችን በቪዲዮና በምስል በማቀናበር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ያጋራል፡፡

መሰል የማነቃቂያ ሃሳቦችን ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማስረጽ አስተሳሰብን በተሻለ ለመቅረጽና ጠንካራ ስብእናን በመሳደግ የነቃ ትውልድ ለመፍጠር መንግሥትና የተለያዩ አካላት እስኪደግፉ መጠበቅ አስፈላጊ ባለመሆኑ ሥልጠናውን በራስ ተነሳሽነትና ያለምንም ክፍያ ለመስጠት መምጣቱን ወጣት ማንያዘዋል ተናግሯል፡፡

ወጣት ማንያዘዋል የተግባቦት አስፈላጊነት፣ የተቃራኒ ጾታና ሌሎች የማኅበራዊ ግንኙነት ክሂሎቶችና ግንዛቤዎች፣ የግለ-ስብእና ግንባታ የግል ተሞክሮ እንዲሁም በተለይ ለወጣቶች የማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ከችግር የሚወጡባቸው አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦች ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
በዕለቱ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ሲኖሩ የነበሩና በአሁኑ ሰዓት በአገር ውስጥ እየሠሩ የሚገኙት ወጣት ከነዓን አሠፋና ወጣት ዮሐንስ ታዬ ልምድና ተሞክሯቸውን አጋርተዋል፡፡